የኮሪደር ልማቱ ድሬዳዋን ለስራና ለኑሮ ተመራጭ አድርጓታል - ኢዜአ አማርኛ
የኮሪደር ልማቱ ድሬዳዋን ለስራና ለኑሮ ተመራጭ አድርጓታል
 
           ድሬዳዋ፤ ጥቅምት 21/2018 (ኢዜአ)፡- የኮሪደር ልማቱ ድሬዳዋ ከተማን ለስራና ለኑሮ ተመራጭ አድርጓታል ሲሉ የድሬዳዋ ነዋሪዎች ተናገሩ።
በከተማዋ በመጀመሪያው ምዕራፍ የተገነባው ከ11 ኪሎ ሜትር በላይ የኮሪደር ልማት ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቋል።
የተገነባውን የኮሪደር ልማት አስመልክተው አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች እንደተናገሩት፤ የኮሪደር ልማቱ የድሬዳዋን ገፅታና ውበት በመጨመር ከተማዋን ለስራና ለኑሮ ተመራጭ አድርጓታል።
                
                
  
ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ሸምሸዲን ፀጋዬ እንደገለፁት፤ የኮሪደር ልማት በከተማዋ አንዳንድ አካባቢዎች የነበረን የቆሻሻ ቦታ በማጽዳት ደህንነቱ የተረጋገጠ አካባቢን ፈጥሯል።
                
                
  
የእግረኛ እና የመኪና መንገዶች ተለይተው መገንባታቸው የትራፊክ ፍሰቱን የተሳለጠ ማድረጉን ጠቅሰው፤ ይህም ለነዋሪዎች ምቹ የስራና መዝናኛ ስፍራ መፍጠሩን አንስተዋል ።
አቶ አዲስ ብርሃኑ በበኩላቸው የኮሪደር ልማቱ የእግረኛ ፣የብስክሌት እና የባቡር መንገዶችን በመለየቱ እንቅስቃሴን ማሳለጡን ገልጸዋል።
                
                
  
ቀደም ሲል ብስክሌት እና መኪና በአንድ መንገድ እየተንቀሳቀሱ አደጋ ሲፈጥሩ የነበረው ሂደትንም መቀረፉን ጠቅሰው ይህ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላቸውን እንደሚወጡ ጠቁመዋል።
ከዚህ ባለፈ በከተማዋ የተገነቡ የመዝናኛ ስፍራዎች ነዋሪዎች የእረፍት ጊዜያቸውን የሚያሳልፉበት ምቹ ስፍራ መፍጠሩን ተናግረዋል ።
ይህ የኮሪደር ልማት እንዲገነባ ላደረጉ መሪዎች ምስጋና ይገባል ብለዋል።
                
                
  
የኮሪደር ልማቱ እሳቸውን ጨምሮ ለሌሎች ሰዎች በጊዜያዊነት እና በቋሚነት የስራ ዕድል መፍጠሩን የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ ቤቲ አለምሸት ናቸው።
ባገኙት የስራ እድልም ልጆቻቸውን እያሳደጉ መሆኑን አንስተዋል።
                
                
  
የከተማው ነዋሪ አቶ ጆርጅ አብደላ በበኩላቸው የኮሪደር ልማቱ ጥሻ የነበሩ አካባቢዎችን ውብና ማራኪ በማድረግ ምቹ የስራና የመኖሪያ ማዕከል እንዲሆን ማስቻሉን ተናግረዋል ።
                
                
  
በድሬዳዋ ከተማ በመጀመሪያ ዙር በአራት አቅጣጫ የተገነባው ከ 11 ኪሎሜትር በላይ የኮሪደር ልማት መጠናቀቁን ከድሬዳዋ አስተዳደር የፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።