የጉባ ላይ ብስራቶች የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ዕድገት በማሳለጥ የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌትነቷን እውን የሚያደርጉ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
የጉባ ላይ ብስራቶች የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ዕድገት በማሳለጥ የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌትነቷን እውን የሚያደርጉ ናቸው
 
           ባሕርዳር ፤ ጥቅምት 21/2018 (ኢዜአ) ፡- በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ የተደረጉት የጉባ ላይ ብስራቶች የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ዕድገት በማሳለጥ የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌትነቷን እውን የሚያደርጉ መሆናቸውን የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ፤ የኢትዮጵያን እድገት እውን በማድረግ በአፍሪካ የግዙፍ ምጣኔ ሃብት ባለቤት የማድረግ እቅድ የሚሳካ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዚህም በሁሉም መስኮች የተሰሩና በመሰራት ላይ ያሉ የልማት ስራዎች ሁነኛ ማረጋገጫ መሆናቸውን ጠቅሰው በሂደት ላይ ያሉ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ደግሞ ቀጣይ እጣ ፈንታዋን የሚወስኑ መሆናቸውን አፅንኦት ሰጥተዋል።
ይህንን በተመለከተ ኢዜአ ያነጋገራቸው የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች፤ የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋ የተደረጉ የጉባ ላይ ብስራቶች የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ዕድገት በማሳለጥ የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌትነቷን እውን የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል።
በአማራ ክልል ፕላንና ልማት ቢሮ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትንተና ዳይሬክተር ይልቃል ሞኜ፤ ኢትዮጵያን የጠንካራ ኢኮኖሚ ባለቤት ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ትልቅ ተስፋ የሰነቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
                
                
  
የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የኢትዮጵያ ማንሰራራት መነሻ መሆኑን ገልጸው፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋ የሆኑት አዳዲስ ፕሮጀክቶች ደግሞ የኢትዮጵያ መሰረታዊ የእድገትና ብልጽግና ብስራቶች ይሆናሉ ነው ያሉት።
የማዳበሪያ፣ የጋዝና የኒውክለር ኢነርጂ፣ የቢሾፍቱ የአውሮፕላን ማረፊያ፣ የነዳጅ ማጣሪያና ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ሲበቁ በመሰረታዊነት ኢትዮጵያን የሚለውጡ እንደሚሆኑ አስረድተዋል።
ፕሮጀክቶቹ ትርፍ ምርት በማምረትና ወደ ውጭ በመላክ ሀገሪቱ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ገቢ እንድታገኝ እንደሚያስችሉም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመሆኑ የሚፈጠረውን የሃይል ፍላጎት ቀድሞ በመተንበይ የኒውክለር ኢነርጂ ማብለያን ለመገንባት መታቀዱ የሚያኮራ ነው ብለዋል።
በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የፐብሊክ ፖሊሲ የሶሰተኛ ዲግሪ ተማሪና የምጣኔ ሃብት ምሁሩ በላይ ስንቴ፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከግብርና መር ፖሊሲ ተላቆ ወደ ብዝሃ ዘርፍ መር መሸጋገሩ ትልቅ እመርታ መሆኑን አንስተዋል።
                
                
  
በዚህም ምክንያት በሀገሪቷ የሚታዩ ለውጦችና ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን አንስተው፤ በጥቂት ዓመታት ውስጥ የላቀ እመርታ እና ማንሰራራት ላይ የምትደርስ ይሆናል ብለዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋ የተደረጉት የጉባ ላይ ብስራቶች ደግሞ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ዕድገት በማሳለጥ የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ማድረግ የሚያስችሉ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በተለይም የማዳበሪያ ፋብሪካው ለግብርናው ዘርፍ ምርታማነት መሰረታዊ ለውጥና ማንሰራራት የሚያመጣ ይሆናል ነው ያሉት።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋ የተደረጉት የጉባ ላይ ብስራቶች የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የኒውክሌር ግንባታ ፕላንት፣ ግዙፉ የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ፣ የ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ቤቶች ግንባታና የጋዝ ልማትን ጨምሮ በድምሩ የ30 ቢሊዮን ብር ፕሮጀክቶች መሆናቸው ይታወቃል።