ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ሀገራዊ መግባባትን የሚፈጥሩ አጀንዳዎች ላይ በማተኮር ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ቅድሚያ ሊሰጡ ይገባል 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 21/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ሀገራዊ መግባባትን የሚፈጥሩ አጀንዳዎች ላይ በማተኮር ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ቅድሚያ ሊሰጡ እንደሚገባ የዘርፉ ምሁራን ገለጹ። 

መገናኛ ብዙኃን የሚያመነጯቸው መረጃዎች ግንዛቤን በመፍጠር፣ የሀገር ገጽታ በመገንባት፣ የዕቅድና ፖሊሲዎችን በማስተዋወቅ ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገትና ብሔራዊ ጥቅም መጠበቅ ቁልፍ ሚና አላቸው።

በዜጎች መካከል የሚንጸባረቁ በብዝኅነት ላይ የተመሰረቱ እሳቤዎች የሚስተናገዱበትን አጀንዳ በመቅረጽም አሰባሳቢ ትርክት ግንባታን በማስተጋባት ብሔራዊ መግባባትን የሚፈጥሩ ወሳኝ መሳሪያዎች ናቸው።

የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም በማስጠበቅ ሀገራዊ መግባባትን ለማጠናከር የመገናኛ ብዙኅን ሙያዊ ሥነ-ምግባርና ኃላፊነት ለዘላቂ ዕድገትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የዘርፉ ምሁራንም መገናኛ ብዙኅን በዜጎች መካከል ሀገራዊ መግባባትን በመፍጠር የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የማስጠበቅ ሙያዊ ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ቤት መምህር ኃይለጊዮርጊስ ማሞ (ዶ/ር)፤ የየትኛውም ዓለም የመገናኛ ብዙኅን የሚሰራው ለተመሰረተበት ሀገር ብሔራዊ ጥቅም መጠበቅ ነው ብለዋል።


 

በኢትዮጵያ ጉዳይ መረጃዎችን የሚያመነጩ መገናኛ ብዙኅንም ዜጎችን የሚያቀራርቡ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ለሀገር ዕድገት መፋጠን አቅም የሚሆኑ ዘርፎች ላይ መስራት እንደሚኖርባቸው መክረዋል።

በዚህም መገናኛ ብዙኅን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት የሚያስከብሩ አጀንዳዎችን በመቅረጽ ለዜጎች ሁለንተናዊ ትሥሥር በከፍተኛ ኃላፊነት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። 

ህዝብና መንግስትን በማቀራረብ የሀገርን የዕድገት ፖሊሲ በማስተዋወቅ የትግበራ ሂደታቸው ለዜጎች ህይወት ሁለንተናዊ ለውጥ መዋሉን ተከታትሎ የማረጋገጥ ስራ ማከናወን እንደሚጠበቅም አንስተዋል።

በዜጎች መካከል ሀገራዊ መግባባትን በማጠናከር መንግስት ለብሔራዊ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ስኬት ድህነትን ለመቀነስ የሚኖራቸውን ጉልህ ፋይዳ ማሳየት እንደሚጠበቅ አስረድተዋል።

በተለይም የኢትዮጵያን ሕጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልከዓ ምድራዊና ኢኮኖሚያዊ የቀይ ባሕር ባለቤትነት ብሔራዊ ጥቅም ላይ ምክንያታዊ ዘገባዎችን ማስተጋባት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።

በሠመራ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚና የጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል መምህር መሐመድ አህመድ፤ ኢትዮጵያዊያን በብሔራዊ ጥቅምና ሀገራዊ ፍላጎቶች ላይ ልዩነት ሊኖረን አይገባም ብለዋል።


 

የኢትዮጵያዊያን የአንድነት አሻራ ያረፈበት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ስኬትም ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር አሰባሳቢ ትርክት መገንቢያ ግዙፍ ብሔራዊና አህጉራዊ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ጥቅም መሠረት የሆነው የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄም የዜጎች የጋራ ብሔራዊ አጀንዳ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በሁሉም የመገናኛ ብዙኅን አማራጮች መረጃን የሚያመነጩና የሚያሰራጩ ዜጎችም ሀገራዊ መግባባትና ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስጠብቁ የልማት አጀንዳዎች ላይ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ መክረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም