በሄይቲ እና ጃማይካ ከባድ አውሎ ነፋስ ባስከተለው ጎርፍ ሳቢያ የበርካቶች ሕይዎት አለፈ - ኢዜአ አማርኛ
በሄይቲ እና ጃማይካ ከባድ አውሎ ነፋስ ባስከተለው ጎርፍ ሳቢያ የበርካቶች ሕይዎት አለፈ
 
           አዲስ አበባ፤ጥቅምት 21/2018 (ኢዜአ)፡-በሄይቲ እና ጃማይካ የተከሰተው ‘ሃሪኬን ሜሊሳ’ የተሰኘው ወጀብና ዝናብ የቀላቀለ ከባድ አውሎ ነፋስ ባስከተለው የጎርፍ መጥለቅለቅ ሳቢያ እስካሁን የ49 ሰዎች ሕይዎት ማለፉ ተሰምቷል።
በሄይቲ የ30 ሰዎች ሕይዎት ማለፉን እና ከ20 በላይ ሰዎች የገቡበት አለመታወቁን የሀገሪቱ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።
እስካሁን ያሉበት ሁኔታ ያልታወቁ ሰዎችን የመፈለጉ ሥራም መቀጠሉን ባለሥልጣናቱ ለአልጄዚራ ገልጸዋል።
                
                
  
ከዚሁ ጋር በተያያዘም የሟቾች ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችል አመላክተዋል።
እንዲሁም የአውሎ ነፋሱ ሰለባ በሆነችው ሌላኛው ሀገር ጃማይካ የ19 ሰዎች ሕይዎት ማለፉን ሮይተርስ ዘግቧል።
እስካሁን ከተመዘገቡት በጣም ኃይለኛ የአትላንቲክ አውሎ ነፋሶች አንዱ እንደሆነ የተነገረለት ሃሪኬን ሜሊሳ በሠዓት 295 ኪሎ ሜትር እንደሚከንፍ ተገልጿል።
አውሎ ነፋሱ የጃማይካን ምዕራባዊ ክልል በመምታት አስከፊ ጉዳት ማድረሱን የሀገሪቱ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
                
                
  
ሃሪኬን ሜሊሳ በካሪቢያን ቀጣና ኩባ፣ሄይቲ እና ጃማይካ በሰው ሕይወት እንዲሁም በንብረት ላይ የከፋ ጉዳት ማድረሱ ተሰምቷል።
ይህን ተከትሎም በካሪቢያን የሚገኙ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ውጭ መሆናቸውን ዘገባው አመላክቷል።
የኤሌክትሪክ አቅርቦቱን ለመመለስና አካባቢዎቹንም የማጽዳት ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙም ተጠቅሷል።