የአፍሪካ ሀገራትን የባቡር ባለሙያዎች የማሰልጠን አቅም ያለው የባቡር ልህቀት ማዕከል ለመገንባት የዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ሀገራትን የባቡር ባለሙያዎች የማሰልጠን አቅም ያለው የባቡር ልህቀት ማዕከል ለመገንባት የዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 21/2018 (ኢዜአ)፡-ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ የአፍሪካ ሀገራት የባቡር ባለሙያዎችን ለማሰልጠን አቅም ያለው የባቡር ልህቀት ማዕከል ለመገንባት የዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አስታወቀ።
በኮርፖሬሽኑ የባቡር አካዳሚ የትምህርትና ስልጠና ክፍል ስራ አስኪያጅ ሲሳይ ጉታ ለኢዜአ እንደገለጹት በቢሾፍቱ ከተማ 62 ሄክታር መሬት ላይ የባቡር ልህቀት ማዕከል ለመገንባት የዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል።
የማዕከሉ የዲዛይንና የአዋጭነት ጥናት መከናወኑን ገልጸው፤ ሌሎች የዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።
በአፍሪካ የልማት አጀንዳ 2063 የተያዘውን አፍሪካን በባቡር ዘርፍ የማስተሳሰር ራዕይ ለማሳካት ከባቡር መስመር ግንባታ እስከ ኦፕሬሽን ባለው ብቃትና ክህሎት ያለው የሰው ሀይል አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።
በማዕከሉ ይህንን ለማሳካት የሚችሉ ኢትዮጵያውያንና ከተለያዩ አፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ባለሙያዎችን ለማሰልጠን መታቀዱን ነው የገለጹት።
ይህም ቀጣናዊ ትስስርን ለማጠናከርና የውጭ ምንዛሬ ገቢን ለማሳደግ እንደሚያስችል ገልጸው፤ የማዕከሉ ግንባታ በመንግስትና በግል አጋርነት እንደሚከናወን ተናግረዋል።
በባቡር ልህቀት ማዕከሉ የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚደረግበትና የባቡር ዘርፉን የሚያሳድጉ ጥናትና ምርምሮች እንደሚከናወኑ ገልጸዋል።
ማዕከሉ የባቡር ጣቢያ፣ 800 ሜትር የሚደርስ የባቡር መሰረተ ልማት፣ ለተግባራዊ ልምምድ አስፈላጊ የሆኑ ቴክኖሎጂና ግብዓቶች እንደሚያካትትም ጠቅሰዋል።
በማዕከሉ ከባቡር ዘርፉ በተጨማሪ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፎች ላይ ባለሙያዎችን ለማሰልጠን መታቀዱንም አክለዋል።
እንደ ሀላፊዋ ገለጻ በባቡር አካዳሚው ባለፉት 13 ዓመታት ከአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲና ከዓለም አቀፍ ዩንቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር በተለያዩ ሙያዎች ስልጠና ሲሰጥ ቆይቷል።
በተፈጠረው የቴክኖሎጂና እውቀት ሽግግር የአዲስ አበባ ቀላል ባቡርና የኢትዮ-ጁቡቲ የባቡር መስመሮች የመስመር ዝርጋታ፣ ጥገና፣ ኦፕሬሽንና ሌሎች ተግባራት በኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች ማከናወን ተችሏል ብለዋል።
በባሌ ሶፍ ዑመር አካባቢ የቱሪዝም ባቡር ሙሉ ለመሉ ስራው በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች መከናወኑን ጠቅሰዋል።