በጂንካ ከተማ የኮሪደር ልማት የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ አስችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በጂንካ ከተማ የኮሪደር ልማት የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ አስችሏል
 
           ጂንካ ፤ ጥቅምት 21/2018 (ኢዜአ)፡-በጂንካ ከተማ የተገነባው የኮሪደር ልማት የተሻለ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር በማድረግ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ማስቻሉን የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስና ነዋሪዎች ገለጹ።
በኮሪደር ልማቱ የእግረኛ መንገድ ከተሽከርካሪ መተላለፊያ መለየቱ ቀደም ሲል በሰዎች ላይ ይደርስ የነበረውን የተሽከርካሪ አደጋ ለመቀነስ ማስቻሉም ተመላክቷል።
                
                
  
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የጂንካ ከተማ ፖሊስ ጽህፈት ቤት የትራፊክ አደጋ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ቡድን መሪ ኢንስፔክተር ባማዮ ይክላ፣ የኮሪደር ልማት ሥራው ከመጀመሩ በፊት እግረኞች ከተሽከርካሪዎች ጋር እየተገፋፉ ይጓዙ ነበር።
በዚህም ምክንያት በተደጋጋሚ የተሽከርካሪ አደጋ ሲከሰት እንደነበር አስታውሰው፤ በተለይ ሕፃናት፣ አዛውንቶች እና አካል ጉዳተኞች ይበልጥ ሲጎዱ እንደነበር ገልጸዋል።
                
                
  
በከተማው የኮሪደር ልማት መገንባቱን ተከትሎ የእግረኛ እና የተሽከርካሪ መንገድ ተለይቶ መሰራቱ የትራፊክ እንቅስቃሴው ጤናማና የተሳለጠ እንዲሆን ማስቻሉን ተናግረዋል።
ይህም ቀደም ሲል በተደጋጋሚ ሲያጋጥም የነበረን የተሽከርካሪ አደጋ ለመከላከል አስችሏል ያሉት ኢንስፔክተር ባማዮ፣ ለዚህም ላለፉት 90 ቀናት በከተማው ምንም አይነት የትራፊክ አደጋ እንዳልተከሰተ በማሳያነት ጠቅሰዋል።
የኮሪደር ልማቱ የአደጋ ስጋት እና የትራፊክ ፖሊሶችን የሥራ ጫና እንዲቀንስ ማድረጉንም ተናግረዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡት የከተማው ነዋሪዎች መካከል ጀማል ኡመር እንዳሉት፣ በከተማው የተገነባው የኮሪደር ልማት እግረኞች እና ተሽከርካሪዎች በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።
                
                
  
ቀደም ሲል "ለተሽከርካሪ አደጋ እንጋለጥ ይሆን" በሚል ስጋት ውስጥ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት ህጻናት፣ አዛውንቶችና አካል ጉዳተኞች ያለስጋት በነጻነት መንቀሳቀስ የሚችሉበት ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል።
የኮሪደር ልማቱ ለከተማው እድገትና ውበት ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የገለጹት የከተማው ነዋሪ መሰለ ወንድሙ በበኩላቸው የኮሪደር ልማቱን ተከትሎ በመንገድ ዳርቻዎች አረንጓዴና የመዝናኛ ስፍራዎች መገንባታቸውን ተናግረዋል ።
                
                
  
የከተማዋ ነዋሪዎች በእግር ተንቀሳቅሰው ጉዳያቸውን ማከናወን የሚችሉበትና በዚያውም ጤናቸውን የሚጠብቁበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም ጠቁመዋል።
በተለይ መንገዱ ለዐይነ ስውራን ልዩ ምልክት ያለው መሆኑ የኮሪደር ልማቱን አካታችና ምቹ አድርጎታል ያሉት ነዋሪው፣ ልማቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
በከተማ አስተዳደሩ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት የመሰረተ-ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም ቡድን መሪ አቶ ፈለቀ ወርቁ በከተማው በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ የኮሪደር ልማት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
                
                
  
በመጀመሪያው ምዕራፍ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ከ2 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍን የኮሪደር ልማት ስራ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት በቅቷል ብለዋል።
የኮሪደር ልማቱ የእግረኛ መንገድ፣ የመዝናኛ ፓርክ፣ የመንገድ አካፋይና ዳርቻ መብራቶችን ጨምሮ መከናወኑንም አስረድተዋል።
በሁለተኛው ምዕራፍ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በተለያዩ የከተማው አካባቢዎች ከስድስት ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍን የተቀናጀ የኮሪደር ልማት ሥራ እንደሚተገበርም አስታውቀዋል።
ለዚህም የወሰን ማስከበር ሥራዎች መጠናቀቃቸውን የጠቀሱት አቶ ፈለቀ የኮሪደር ልማቱ ከተማዋን ለማዘመን፣ ዕድገቷን ለማፋጠንና ተወዳዳሪነቷን ለመጨመር እያገዘ መሆኑ ተናግረዋል።