የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የቤት ባለቤት አድርጎናል - ኢዜአ አማርኛ
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የቤት ባለቤት አድርጎናል
 
           አሶሳ፤ ጥቅምት 21/2018(ኢዜአ)፦ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ያለባቸውን የኢኮኖሚ ችግር በማቃለል የቤት ባለቤት እንዲሆኑ እንዳገዛቸው በአሶሳ ከተማ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ተናገሩ።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የክረምት ወራትና የበጋ ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየተለመደ ከመምጣቱ ባለፈ የብዙዎችን ችግር እያቃለለ ይገኛል።
በአሶሳ ከተማ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል የወረዳ ሁለት ነዋሪዋ ወይዘሮ በሂዳ አብዱልባጊ ከዚህ በፊት የነበረው የመኖሪያ ቤታቸው ያረጀ በመሆኑ በክረምት እና በበጋ ወቅት ከባድ ጊዜን እንዲያሳልፉ የሚያደርግ እንደነበር ያስታውሳሉ።
                
                
  
ይህም ጤናቸው እንዲታወክ እና ለተለያዩ በሽታዎች እንዲጋለጡ ያደርጋቸው እንደነበር ገልጸዋል።
አሁን ግን የክልሉ መንግስት ተቋማት በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለአረጋውያን እና አቅመ ደካሞች የቤት ግንባታ እና እድሳት በማከናወናቸው ቤታቸው በአዲስ መልክ ተገንብቶ ለኑሮ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው በደስታ ስሜት ተናግረዋል።
" በአጭር ጊዜ ይህንን ቤት ይገነቡልኛል ብዬ አላሰብኩም ነበር" የሚሉት ወይዘሮ በሂዳ ቃላቸውን አክብረው በአጭር ጊዜ ውስጥ የቤት ባለቤት አድርገውኛል ብለዋል።
መንግስት ለአቅመ ደካሞች የሚያደርገው ዕገዛ የሚያስመሰግን እና ሊጠናከር ይገባል ነው ያሉት።
                
                
  
አራት ልጆችን ብቻቸውን እያሳደጉ የሚገኙት የወረዳው ነዋሪ ወይዘሮ ሱጉ ሳሚ የተገነባላቸው ቤት ከብዙ ስቃይ እና መከራ እንደታደጋቸው ጠቁመዋል።
                
                
  
"ከዚህ በፊት ቤት ለመስራት አቅም ስላልነበረን ብዙ ፈተና አሳልፈናል" የሚሉት ወይዘሮ ሱጉ የተገነባላቸው ቤት ለሁሉም ነገር ምቹ ነው ብለዋል።
በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 210 አዳዲስ ቤቶች እና 341 ዕድሳት የተደረገላቸው ቤቶችን ለነዋሪዎች ማስረከብ መቻሉን የተናገሩት ደግሞ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ገለታ ሀይሉ ናቸው።
                
                
  
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በየዓመቱ እየተጠናከረ መምጣቱን የተናገሩት አቶ ገለታ በዘንድሮው ዓመት የክልሉ የመንግሥት ተቋማት የአረጋውያን እና አቅመ ደካሞች ቤት ግንባታ ላይ በተጠናከረ ሁኔታ መሳተፋቸውን ገልጸዋል።
በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በክልሉ የመንግስት ተቋማት ብቻ 108 ቤቶችን ዕድሳት እና ግንባታ ለማከናወን ታቅዶ እስካሁን ከ70 በላይ ቤቶች ተጠናቀው ለተጠቃሚዎች መተላለፋቸውን ጠቁመዋል ።