የአኙዋ ባዮስፌር በዩኔስኮ መመዝገቡ ኢትዮጵያ በብዝሃ ሕይወት ጥበቃና በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂዎች ስኬት እያስመዘገበች ለመሆኑ ሁነኛ ማሳያ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአኙዋ ባዮስፌር በዩኔስኮ መመዝገቡ ኢትዮጵያ በብዝሃ ሕይወት ጥበቃና በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂዎች ስኬት እያስመዘገበች ለመሆኑ ሁነኛ ማሳያ ነው
 
           አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 21/2018 (ኢዜአ)፡-የአኙዋ ባዮስፌር በዩኔስኮ በሰውና ባዮስፌር (ማፕ) መርሃ ግብር መመዝገቡ ኢትዮጵያ በብዝሃ ሕይወት ጥበቃና በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂዎች ስኬት እያስመዘገበች ለመሆኑ ሁነኛ ማሳያ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ገለጹ።
ባዮስፌር ሪዘርቭ ሰውና ተፈጥሮን አስማምቶ ማኖር የሚያስችል የጥበቃ ስልት ነው።
በጋምቤላ ክልል የሚገኘው የአኙዋ ባዮስፌር ሪዘርቭ በመስከረም ወር 2018 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ስድስተኛው የባዮስፌር ሪዘርቭ በመሆን በዩኔስኮ ተመዝግቧል።
ባዮስፌሩ ስድስት የተለያዩ ሥነ-ምህዳሮችን ያካተተ ሲሆን እርጥብ የአፍሮ-ሞንታኔ ደኖች፣ የሽግግር የዝናብ ደኖች፣ የወንዝ ዳር እፅዋት፣ ረግረጋማ ቦታዎች እና ዛፍ የበዛባቸው ሳቫናዎች ይገኙበታል።
                
                
  
የባዮስፌሩ መመዝገብ የሀገሪቱን የጥብቅ ቦታ ሽፋን የሚያሳድግና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና ልማት ሥራን ለዓለም ለማጋራት የሚያስችል መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት የደንና ግጦሽ መሬት ብዝሃ ሕይወት ምርምር መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አበራ ስዩም ለኢዜአ እንዳሉት፤ ባዮስፌር ለተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና ለሰዎች የልማት ተጠቃሚነት ሚና አለው።
                
                
  
ይህም ብዝሃ ሕይወትን ለመጠበቅ፣ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥና ምርምርና ጥናት ለማካሄድ ሥራ ላይ ይውላል ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት የአኙዋ ባዮስፌር ሪዘርቭን ለማስመዝገብ ሲሠራ መቆየቱን አንስተው፤ ዘንድሮ በቻይና በተካሄደው ጉባዔ በዩኔስኮ ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል።
የአኙዋ ባዮስፌር ሪዘርቭ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር በላይ ስፋት ያለው፣ እምቅ የብዝሃ ሕይወት ሃብትና የማኅበረሰብ ተፈጥሮን የመጠበቅ ባህልን አጣምሮ የያዘ የጥበቃ ስፍራ ነው ብለዋል።
የአኙዋ ባዮስፌር ሪዘርቭ መመዝገብ የሀገሪቷን ጥብቅ ቦታዎች አሁን ካለበት 12 በመቶ ወደ 30 በመቶ በማሳደግ ዓለም አቀፍ ግብ ለማሳካት እገዛ ያለው መሆኑን አቶ አበራ ተናግረዋል።
                
                
  
የአኙዋ ባዮስፌር መመዝገብ ኢትዮጵያ ያላትን ፀጋ ለዓለም ይዛ የቀረበችበትና ለሀገር ገጽታ ግንባታ ትልቅ አስተዋፅኦ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ያላትን ምቹ ፖሊሲ፣ የብዝሃ ሕይወት ሃብትና የማኅበረሰብ ዕውቀት በማቀናጀት የተፈጥሮ ሃብት በመጠበቅ ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ ያስቻላትን ልምድ ለዓለም የምታካፍልበት መሆኑንም አብራርተዋል።
የአኙዋ ባዮስፌር መመዝገብ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም እና ኢትዮጵያ ለያዘችው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ጠቀሜታ ያለው መሆኑንም ተናግረዋል።
በተያዘው የ2018 በጀት ዓመት ሁለት ተጨማሪ ባዮስፌር ሪዘርቮችን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
                
                
  
የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኩመራ ዋቅጅራ በበኩላቸው፤ የአኙዋ ባዮስፌር ሪዘርቭ መመዝገብ የአገሪቱን የጥበቃ ቦታ ሽፋን የሚያሳድግ ነው ብለዋል።
የአኙዋ ባዮስፌር፣ የካፋ፣ የሸካ፣ የያዩ፣ የጣና ሐይቅ እና የመጀንግ ደን ባዮስፌር ሪዘርቮችን በመቀላቀል በዩኔስኮ እውቅና ያገኘ የኢትዮጵያ ስድስተኛው ባዮስፌር ሪዘርቭ ነው።