ቀጥታ፡

ከንጋት ሃይቅ የሚገኘውን የዓሳ ሃብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችል መመሪያ ተዘጋጅቷል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 21/2018 (ኢዜአ)፡-ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ንጋት ሃይቅ የሚገኘውን የዓሳ ሃብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችል መመሪያ መዘጋጀቱን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ ገለጹ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያዊያን እውቀት፣ ጉልበትና ጥሪት ተገንብቶ ለስኬት የበቃ ታላቅ ፕሮጀክት ነው።

የህዳሴ ግድብ ግንባታ እውን መሆን ለኢትዮጵያ እድገትና ማንሰራራት አዲስ የታሪክ ምእራፍ የከፈተ የሀገር ሃብት መሆኑም ይታወቃል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ትሩፋት የሆነው ንጋት ሃይቅ ለዓሳ ምርትና ምርታማነት መጨመርና ለአካባቢው ተጨማሪ የኢኮኖሚ አቅም እየሆነ መጥቷል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤  በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ የተንጣለለውና ንጋት ሃይቅ በሚል የተሰየመው የውሃ ሃብት ከሌሎች ወንዞች ጋር ያለው ተፈጥሯዊ ግንኙነት ላቅ ያለ ነው።


 

በዚህም ሃይቁ በርካታ ተፈጥሯዊ ንጥረ ነገር በውስጡ የያዘ መሆኑ ለዓሳ ሃብት ልማት ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል ብለዋል።  

በአሁኑ ወቅት ንጋት ሐይቅ 15 ሺህ ቶን ዓሳ የማምረት አቅም እንዳለው የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ይህም ለአካባቢው ማህበረሰብ ትልቅ የስራ እድል ይዞ መምጣት መቻሉን አብራርተዋል።

ከንጋት ሃይቅ የሚገኘውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ በዘላቂነት ለማረጋገጥ ግብርና ሚኒስቴር ጥናት ማካሔዱን ገልጸዋል።

በዚህም ሀይቁን ከተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች መከላከል አንዱና ዋነኛው መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የሀይቁን የደህንነት ስጋት ተጋላጭነት ቀድሞ መከላከል የሚያስችል መመሪያ መዘጋጀቱን አብራርተዋል።

መመሪያው ዓሳ ማስገር የሚከናወንበትን፣ የዝርያ ማሻሻያ ስራዎችና የዓሳ መረብ አጠቃቀምን ማሻሻል የሚያስችል አሰራር የተካተተበት ስለመሆኑ አስረድተዋል።

በተጨማሪም የገበያ ትስስር በመፍጠር ከንጋት ሃይቅ የሚገኘውን የዓሳ ሃብት በአግባቡ ለገበያ ማቅረብ እንዲቻል የሚያግዝ አሰራርም እንዲሁ በመመሪያው ለማካተት ጥረት መደረጉን አብራርተዋል።


 

በዓሳ ምርትና ምርታማነት ዙሪያ ከሚሰሩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር ማጠናከር ላይም ትኩረት መደረጉን ጠቁመዋል።

በተለይም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የምርምር ማዕከላት በመመሪያው አተገባበር ዙሪያ በጥናት የተደገፈ ግብዓት እንዲያቀርቡ በማድረግ በጥናት ላይ የተመሰረተ አቅጣጫ ተቀምጧል ነው ያሉት። 

በአሁኑ ወቅት ንጋት ሃይቅን ተከትሎ በዓሳ ማስገር ስራ ላይ የተሰማሩ 78 ማህበራት የተደራጁ ሲሆን 35ቱ በሙሉ አቅማቸው እየሰሩ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በአጠቃላይ 866 በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች የማህበራቱ አባል በመሆን የስራ እድል ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም