ኢትዮጵያ ገቢራዊ ያደረገቻቸው ፕሮጀክቶች ለቀጣናዊ የኢኮኖሚ ውህደት ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር ያሳየ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ገቢራዊ ያደረገቻቸው ፕሮጀክቶች ለቀጣናዊ የኢኮኖሚ ውህደት ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር ያሳየ ነው
 
           አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 21/2018 (ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ገቢራዊ ያደረገቻቸው ፕሮጀክቶች ለቀጣናዊ የኢኮኖሚ ውህደት ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር ያሳየ ነው ሲሉ አፍሪካዊያን ምሁራን ገለጹ።
ፕሮጀክቶቹ አፍሪካን እና ቀጣናውን በኢኮኖሚ ለማስተሳሰር ጉልህ ፋይዳ እንዳላቸውም ምሁራኑ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብ በዜጎች ርብርብ በራስ አቅም ገንብታ አጠናቃለች።
የኒውክሌር ኃይልን ለሠላማዊ ግልጋሎት ለማዋል የሚያስችል ፕሮጀክት፣የነዳጅ ማጣሪያ እና የተፈጥሮ ጋዝና ግዙፍ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ለማካሄድ ተግባራዊ እርምጃዎችንም ወስዳለች።
በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ዩኒቨርስቲ የአፍሪካ-ቻይና ጥናት ማዕከል ዳይሬክተር ዴቪድ ሞኛዬ(ፕ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው መስክ እየተገበረቻቸው ያሉ የልማት ኢኒሼቲቮች ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ ናቸው።
                
                
  
ከመሰረተ ልማት አቅርቦት አኳያም በአዲስ አበባ የታየው ለውጥ የሚደነቅ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም የውጤታማ አመራር መኖር ማሳያ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብ በራስ አቅም ገንባታ እውን ማድረጓ ትልቅ እርምጃ መሆኑን የገለጹት ፕሮፌሰሩ ቀጣናውን በኃይል ለማስተሳሰር ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከድህነት ለመላቀቅ በምግብ ዋስትና በኃይል አቅርቦት ላይ ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች ከኢትዮጵያ አልፎ በቀጣናው ሀገራት በጎ ተጽዕኖ ያላቸው መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ የልማት ኢኒሼቲቭ ከአፍሪካ አጀንዳ 2063 ጋር የተሳሰረ መሆኑን ገልጸው፤ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ሞዴል ሆኖ የሚያገለግል ነው ብለዋል።
                
                
  
በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የፖሊሲ ተንታኝ ፓ ኪዌሲ ሄቶ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ከኃይል አቅርቦት ባለፈ ማዳበሪያን በሀገር ውስጥ ለማምረት እንቅስቃሴ መጀመሯ ትልቅ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የልማት ኢኒሼቲቮች ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ኢኮኖሚ መለወጥ አዎንታዊ ሚና እንዳላቸውም አብራርተዋል።