ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር ) ለምክር ቤት አባላት የሰጡት ማብራሪያ የትግራይ ክልል ህዝብን የሰላምና የልማት ፍላጎት በትክክል ያመላከተ ነው- የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች

መቀሌ ፤ ጥቅምት 21/2018 (ኢዜአ)፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለምክር ቤት አባላት የሰጡት ማብራሪያ የትግራይ ክልል ህዝብን የሰላምና የልማት ፍላጎት በትክክል ያመላከተ መሆኑን የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወቃል። 

በተለይም በሰላምና ጸጥታ ጉዳይ ላይ በትግራይ ክልል ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ እና መንግስት ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በተመለከተ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው የትግራይ ክልል ህዝብ ፍላጎት ዘላቂ ሰላም እና የልማት ተጠቃሚነት መሆኑን ገልጸው የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተከትሎ በዚህ የፌዴራል መንግስት ብዙ መስራቱን አንስተዋል። 

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤት አባላት የሰጡት ማብራሪያ የትግራይ ክልል ህዝብን የሰላምና የልማት ፍላጎት በትክክል ያመላከተ መሆኑን ገልጸዋል። 

ከነዋሪዎቹ መካከል ወጣት ይልማ ሃብቴ፣ አቶ አፅበሃ አብርሃ እና መምህር ሃይለ ከለለው፤ የትግራይ ክልል ህዝብ ለግጭትና ለጦርነት የሚሰሩ አካላትን በፍጹም አይቀበልም ብለዋል። 


 

የህዝቡ ፍላጎት ከምንም በላይ ሰላም እና ልማት መሆኑን ተናግረው ይህንን ፍላጎቱን በአግባቡ ተገንዝቦ የሚሰራለት አስተዳደር የሚሻ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም የወጣቱ ፍላጎት ሰርቶ መለወጥና ህይወቱን በአግባቡ መምራት መሆኑን የተናገረው ወጣት ይልማ፤ በክልሉ ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችና የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቋል። 

የትግራይ ክልል ህዝብ ፍላጎት ሰላሙን በመጠበቅ ለሀገር ልማት በጋራ መስራትና መጠቀም በመሆኑ ለተግባራዊነቱ የድርሻችንን ለመወጣት እንሰራለን ብሏል። 

በመቀለ የዓዲሐ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ሃይለ ከለለው በበኩላቸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለልማት ስኬት እና ለሰላም ግንባታ እያደረጉት ያለው ቀናኢነት የሚደነቅ ነው ብለዋል። 


 

የትግራይ ክልል ህዝብም የሚሻው ይህንኑ መሆኑን ያነሱት መምህሩ የህዝቡን ፍላጎት በተረዳ መልኩ ለምክር ቤቱ የሰጡት ማብራሪያ ተገቢና ትክክለኛ መሆኑን ገልጸዋል። 

ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ አፅበሃ አብርሃ፤ በሁሉም መልኩ የኢትዮጵያን እድገትና ብልጽግና እውን ለማድረግ መንግስት እያከናወናቸው ያሉ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች ትልቅ ተስፋ የተሰነቀባቸው መሆኑን ተናግረዋል።


 

በመሆኑም በሁሉም አካባቢዎች ሰላምን በማጽናት ልማትን በማስቀጠል የጋራ ልማትና ተጠቃሚነታችንን እውን ለማድረግ እንሰራለን ብለዋል። 

ከትግራይ ክልል ጋር በተገናኘ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት ማብራሪያም የክልሉን ህዝብ የሰላምና የልማት ፍላጎት መሰረት ያደረገ እና ትክክለኛ ምልከታ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም