የባሕር በር ጉዳይ ምላሽ ማግኘት ያለበት የጋራ ጥያቄያችን ነው- የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
የባሕር በር ጉዳይ ምላሽ ማግኘት ያለበት የጋራ ጥያቄያችን ነው- የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት
 
           ባሕር ዳር፤ ጥቅምት 21 /2018(ኢዜአ)፡ - የባሕር በር ጥያቄ የሀገር ህልውና እና የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ በመሆኑ ምላሽ ማግኘት ያለበት የጋራ ጥያቄያችን ነው ሲል የአማራ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ።
የአማራ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሀይል ንቅናቄ (አዴሀን) ሊቀመንበር ተስፋሁን አለምነህ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የባሕር በር ጥያቄ የሀገር ህልውና እና የብሄራዊ ጥቅም ጉዳይ በመሆኑ ምላሽ ማግኘት ያለበት የጋራ ጥያቄያችን ነው ብለዋል።
የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ቢኖርም በሀገር ብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ የተለየ አቋም የሌላቸው መሆኑን አንስተው በዚህ ረገድ መንግስት የጀመረውን እንቅስቃሴና የያዘውን አቋም እናደንቃለን እንደግፋለንም ሲሉ አረጋግጠዋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ የጋራ ምክር ቤቱ በቅርበት እንደሚሰራ እና ህብረ ብሄራዊ አንድነቷና ብሔራዊ ጥቅሟ የተከበረች ሀገር ለልጆቻችን ለማስረከብ እንሰራለን ብለዋል።
እንደፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለሰላም መስፈን፣ ለሕግ መከበርና ሌሎች የውስጥ ጉዳዮች ላይ በጋራ እንደምንሰራ ሁሉ በብሔራዊ ጥቅሞችና ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ በጋራ መስራት ግዴታቸን ነው ብለዋል።
መንግስት የባሕር በር ባለቤትነትን ለማረጋገጥ ሲሰለፍ በተቃርኖ መቆም በታሪክ ተወቃሽ የሚያደርግና ለሕሊናም ሰላምን የሚነሳ መሆኑን አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከቀናት በፊት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ፤ የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ የማይቀር ስለመሆኑ አስረግጠው መናገራቸው ይታወሳል።