የአፍሪካ ህብረት የ30 ቢሊዮን ዶላር የአቪዬሽን መሰረተ ልማት የኢንቨስትመንት እቅድ ይፋ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ህብረት የ30 ቢሊዮን ዶላር የአቪዬሽን መሰረተ ልማት የኢንቨስትመንት እቅድ ይፋ አደረገ
 
           አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 21/2018 (ኢዜአ):-የአፍሪካ ህብረት የአህጉሪቷን የአቪዬሽን መሰረተ ልማት ማዘመንን አላማ ያደረገ የ30 ቢሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት እቅድ ዛሬ ይፋ አድርጓል።
ከጥቅምት 18 ቀን 2018 ዓ.ም አንስቶ በአንጎላ ሉዋንዳ ሲካሄድ የነበረው ሶስተኛው የአፍሪካ መሰረተ ልማት ፋይናንስ ጉባኤ ዛሬ ተጠናቋል።
በጉባኤው ላይ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ፣ የአንጎላ ፕሬዝዳንት እና የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር ጆአኦ ሎሬንቾ፣ የህብረቱ ተቋማት አመራሮች፣ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ የአየር መንገዶች ዋና ስራ አስፈጻሚዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ከጉባኤው ጎን ለጎን በአፍሪካ ነጻ የአየር ትራንስፖርት ገበያ አማካኝነት የአህጉሪቷን አቪዬሽን መሰረተ ልማት በፋይናንስ በመደገፍ እና በማዘመን የተቀናጀ የአየር አገልግሎት እና ነጻ እንቅስቃሴን መፍጠር ላይ ያተኮረ ከፍተኛ የምክክር መድረክ ተከናውኗል።
የአፍሪካ ህብረት የመሰረተ ልማት እና ኢነርጂ ኮሚሽነር ሌራቶ ማታቦጅ በመድረኩ ላይ በአየር ትራንስፖርት ገበያው አማካኝነት የአህጉሪቷን የአቪዬሽን መሰረተ ልማት ለማዘመን የሚውል የ30 ቢሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት እቅድ ዛሬ ይፋ አድርገዋል።
እቅዱ አፍሪካ በቀጣይ 10 ዓመት የአቪዬሽን ዘርፉን ለማሻሻል የሚያስፈልጋትን ከ25 እስከ 30 ቢሊዮን ዶላር የፋይናንስ ክፍተት የሚሞላ እንደሆነ ኢዜአ ከአፍሪካ ህብረት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
በአፍሪካ እ.አ.አ በ2024 160 ሚሊዮን የነበረው የመንገደኞች መጠን እ.አ.አ በ2050 ወደ 500 ሚሊዮን ገደማ እንደሚደርስ የገለጸው ህብረቱ ኢንቨስትመንቱ የተሳፋሪዎችን ደህንነት ለማረጋገጥ እና አቅምን ለማጎልበት እንደሚያስችል አመልክቷል።
በኢንቨስትመንት እቅዱ አማካኝነት ገንዘቡ ለአውሮፕላን ማረፊያ፣ አውሮፕላን ጣቢያ እና ጥገና ማዕከላት መሰረተ ልማት፣ የአቪዬሽን ስርዓቶች ማዘመን፣ ለሰው ኃይል ልማት፣ ለቁጥጥር ስራ፣ ለቴክኖሎጂ እና ተጓዳኝ ስራዎች እንደሚውል ተገልጿል።
የአፍሪካ ህብረት 10 ቢሊዮን ዶላሩን ከአፍሪካ መንግስታት፣ ከቀጣናዊ የልማት ባንኮች እና ከባለቡዙ ወገን አጋሮች ለመሰብሰብ መታቀዱን አስታውቋል።
ቀሪው 20 ቢሊዮን የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ አጋሮች፣ የሉዓላዊ ሀብት ፈንዶች (sovereign wealth funds) እና የጡረታ ፈንዶችን ጨምሮ ከግል እና የተቋማት ኢንቨስተሮች ለማግኘት መታሰቡን ነው ያመለከተው።
የሀብት ማሰባሰቡ የሚከናወነው በአፍሪካ ነጻ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ማዕቀፍ ሲሆን የ30 ቢሊዮን ዶላሩ ከእ.አ.አ 2025 እስከ 2035 ለሚተገበሩ ስራዎች የሚውል ነው።
የአፍሪካ ህብረት የመሰረተ ልማት እና ኢነርጂ ኮሚሽነር ሌራቶ ማታቦጅ አቪዬሽን የትራንስፖርት አማራጭ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ትስስር ስትራቴጂካዊ ሞተር እንዲሁም የአጀንዳ 2063 እና የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ቁልፍ አቅም ነው ብለዋል።
በኢንቨስትመንት እቅዱ የሚሰሩ ፕሮጀክቶች ዓለም አቀፍ የአረንጓዴ ልማት መመዘኛዎችን ባሟላ እና ከካርቦን ልህቀት ነጻ በሆነ መልኩ እንደሚገነቡ አመልክተዋል።
ህብረቱ ዘመናዊ፣ ውጤታማ እና ዘላቂ የአቪዬሽን ኔትወርክ በመፍጠር ለአፍሪካ የኢኮኖሚ ትስስር ለማጠናከር፣ የአየር ትራንስፖርት ግንኙነት ስር እንዲሰድ እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት እንዲያድግ በቁርጠኝነት ይሰራል ነው ያሉት።