ቀጥታ፡

ዜጎች ወደ ውጭ ሀገር ለሥራ እንልካለን ከሚሉ አጭበርባሪዎች ራሳቸውን እንዲጠብቁ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 21/2018 (ኢዜአ)፡- ሕጋዊ መሠረትም ሆነ ከውጭ ሀገራት ጋር ውል ሳይኖራቸው ‘ወደ ውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት እንሰጣለን’ እያሉ በሚያጭበረብሩ አካላት እንዳይታለል ዜጎች ራሳቸውን መጠበቅ እንደሚገባቸው ተገለጸ።

የውጭ ሀገራት ሥራ ስምሪት የሚሰጠው በሥራና ክኅሎት ሚኒስቴር አማካኝነት ብቻ መሆኑም ተገልጿል።

በዚህም መሠረት ዜጎች ካሉበት ሆነው ለውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት መመዝገብ የሚችሉበት የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት https://lmis.gov.et/ ተዘርግቶ እየተሠራ መሆኑ ተጠቁሟል።

ይህን ተከትሎም ኢትዮጵያ ስምምነት ወደ ፈረመችባቸው ሥድስት የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ለመሄድ የሚስችሉ ስልጠናዎችና ምዘናዎች ከተከናወኑ በኋላ ስምሪቱ እንደሚሰጥ ተመላክቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከመንግሥት ዕውቅናና ፈቃድ ውጭ ወደ ውጭ ሀገራት የሚደረግ የሥራ ስምሪት አለመኖሩን በመገንዘብ፤ ዜጎች ሕይወታቸውን፣ ጊዜያቸውን ብሎም ገንዘባቸው ከማጣት እንዲቆጠብ ተጠይቋል።

በሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ደላላዎች የሚደረግ የውጭ ሀገር ጉዞ የራስን ብሎም የቤተሰብን ኑሮ ለከፋ ችግር እንደሚያጋልጥ ተገንዝቦ ከዚህ አደገኛ አካሄድ እንዲቆጠብ መክረዋል።

የሥራና ክኅሎት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አበበ ዓለሙ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በሀገር ውስጥ ያሉ ፀጋዎችን መሠረት ያደረገ የሥራ ዕድል ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እየተሠራ ነው ብለዋል።

የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ካስፈለገም በሚኒስቴሩ አማካኝነት በተዘረጉ አሠራሮች በየወረዳቸው በሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛዎች በመሰልጠን ደኅንነታቸው ብሎም ተጠቀሚነታቸው ተጠብቆ ስምሪቱን የሚያገኙበት ሁኔታ እንዳለ አስረድተዋል።

ከውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ጋር በተያያዘ መረጃዎችን ለማግኘት በ9138 ነጻ የስልክ መስመር መደወል እንደሚቻልም አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም