ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ መድን በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ምድቡን መቀላቀል ሳይችል ቀርቷል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 20/2018 (ኢዜአ):- ኢትዮጵያ መድን በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ሁለተኛ ዙር ከወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ ፒራሚድስ ጋር ዛሬ ባደረገው የመልስ ጨዋታ 2 ለ 0 ተሸንፏል።

ማምሻውን በጁን 30 ኤር ዲፌንስ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ሙስጠፋ ዚኮ እና ኤወርተን ዳ ሲልቫ ግቦቹን ከመረብ ላይ አሳረፈዋል።

ውጤቱን ተከትሎ ፒራሚድስ በድምር ውጤት 3 ለ 1 በማሸነፍ ምድብ ድልድሉን መቀላቀል ችሏል።

ክለቦቹ ጥቅምት 16 ቀን 2018 ዓ.ም ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ አንድ አቻ መለያየታቸው የሚታወስ ነው።

ኢትዮጵያ መድን የመጀመሪያ የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎው ሁለተኛ ዙር ላይ ተገቷል።

ቡድኑ አምናው በታሪኩ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን ማሸነፉን ተከትሎ ነው በአህጉራዊ መድረክ የመሳተፍ እድል ያገኘው።

የግብጹ ፒራሚድስ ክለብ የወቅቱ የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የዋንጫ ባለቤት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም