የወራቤ ግብርና ምርምር ማዕከል የአካባቢውን አርሶ አደሮች ይበልጥ ውጤታማ እያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የወራቤ ግብርና ምርምር ማዕከል የአካባቢውን አርሶ አደሮች ይበልጥ ውጤታማ እያደረገ ነው
 
           ወራቤ ፤ ጥቅምት 20/2018 (ኢዜአ):- የወራቤ ግብርና ምርምር ማዕከል የተሻሻሉ ዝርያዎችን በማቅረብ እና በሙያ ያደረገላቸው ድጋፍ የግብርና ልማታቸውን ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን እያገዛቸው መሆኑን በስልጤ ዞን የአሊቾ ውሪሮ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የወራቤ ግብርና ምርምር ማዕከል በዘር ብዜት፣ በምርምርና በቴክኖሎጂ ሽግግር የምግብ ማጠናከሪያ ፕሮግራም ድጋፍ የተከናወኑ ሥራዎች በስልጤ ዞን አሊቾ ውሪሮ ወረዳ በመስክ ተጎብኝቷል፡፡
                
                
  
በዚህ ወቅት በወረዳው የሽልማት ቀበሌ አርሶ አደር ነስራ ከማል በሰጡት አስተያየት፤ ከዚህ ቀደም የግብርና ሥራቸውን በባህላዊ መንገድ ስለሚያከናውኑ በልፋታቸው ልክ ውጤታማ ሳይሆኑ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡
                
                
  
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በምርምር ማዕከሉ የሚቀርበውን የሰብል ምርጥ ዘርና ሌሎች የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን በባለሙያዎች ታግዘው በመተግበር ምርታማነታቸው እያደገ መምጣቱንም ተናግረዋል፡፡
በዚህም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው እየተሻሻለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ማዕከሉ በሰብል ዝርያና በሙያ በሚያደርግላቸው ድጋፍ ውጤታማነታቸው እያደገ መምጣቱን የተናገሩት ሌላው አርሶ አደር ናሲያ ጃቢር ናቸው፡፡
                
                
  
በተለይ በመስመር መዝራትን ጨምሮ ሌሎች የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን ተጠቅመው ከሚያለሙት ገብስ፣ ስንዴና አተር የተሻለ ምርት እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
                
                
  
ዝርያዎቹ ፈጥነው ከመድረስ ባለፈ በምርት ይዘታቸው ከፍተኛና በሽታ መቋቋም የሚችሉ ናቸው ያሉት አርሶ አደሩ፤ በመሥመር መዝራቱም በተለምዶ በብተና ከሚደረገው አዘራር በተሻለ ውጤታማ እንዲሆኑ ያገዛቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትልና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አለምይርጋ ወልደሥላሴ በወቅቱ እንዳሉት፤ የምርምር ማዕከሉ በክልሉ ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እያገዘ ነው፡፡
                
                
  
በዚህም በሌማት ትሩፋትና በአካባቢ ጥበቃ ሥራው ተስፋ ሰጪ ውጤት እየተመዘገበ ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡
በምርምር ማዕከሉ እገዛ እየተገኙ ያሉ ስኬቶችን የማስፋት ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
ጉብኝቱ የምርምር ማዕከሉ ግብርናውን ለማዘመን የሚያከናውናቸው ሥራዎችን ለባለድርሻ አካላት የማሳወቅ፣ ግብዓት የማግኘትና ተሞክሮ መለዋወጥን ዓላማ ያደረገ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጌታሁን ያዕቆብ (ዶ/ር) ናቸው፡፡
                
                
  
ማዕከሉ የስንዴ፣ ገብስ፣ ቦሎቄ፣ ተልባ፣ እንሰትና የእንስሳት ዝርያን ማሻሻል ጨምሮ ግብርናን ለማዘመንና ምርታማነት ለማሻሻል የሚያግዙ ተግባራት ላይ አተኩሮ እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በጉብኝቱ ላይ የክልሉ ግብርና፣ ምርምር ኢንስቲትዩት ከፍተኛ አመራሮች እና አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል፡፡