ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሟን እና ህልውናዋን ለማስጠበቅ ወደነበረችበት ቀይ ባህር መመለሷ ግድ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 20/2018(ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሟን እና ሕልውናዋን ለማስጠበቅ ወደነበረችበት ቀይ ባህር መመለሷ ግድ ነው ሲሉ ፕሮፌሰር ብሩክ ሀይሉ በሻህ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ የቀይ ባህር ጉዳይ ሕጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልክዓ ምድራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በኢትዮጵያና አሜሪካ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ብሩክ ሀይሉ በሻህ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ  ከባህር በር በ60 ኪሎሜትር ርቀት የበይ ተመልካች ለመሆን ተገዳለች፡፡

ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር የተገለለችበት መንገድ ህጋዊ መሰረት የሌለው መሆኑን በማንሳት፤ ባህር በር አልባ ከሆኑ 44 ሀገራት ሰፊ የህዝብ ቁጥር እንዳላትም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለቀይ ባህር ቀጣና አዲስ አይደለችም ያሉት ፕሮፌሰር ብሩክ፤ ከፐርሺያ እስከ ባበል መንደብና ሕንድ የሚቀዝፉ ጠንካራ መርከቦች እንደነበሯት አስታውሰዋል፡፡

የቀይ ባህር ባለቤት በነበረችበት ወቅት ከሮማና ግሪክ ግዛቶች ጋር ጠንካራ የንግድ ትስስር እንደነበራት ገልጸው፤ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ጥቅምና ሀገራዊ ህልውና ለማስጠበቅ ወደ ቀይ ባህር መመለስ ግድ ነው ብለዋል፡፡ 

ኢትዮጵያ በትብብር ላይ የተመሰረተ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ እንዳላት በመጥቀስ፤ ወደ ቀይ ባህር መመለስ ለቀጣናው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

በዓለም ላይ የባህር በር ከሌላቸው ሀገራት መካከል 16ቱ በአፍሪካ እንደሚገኙ ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ከ34 ዓመት በፊት ሁለት ሺህ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባህር በር ባለቤት ነበረች ብለዋል፡፡

ከአፍሪካ ዙምባብዌና ማላዊ የሞዛምቢክን የባህር በር እንደሚጠቀሙ አስታውሰው፤ ኢትዮጵያ ያቀረበችው ሰላማዊና ህጋዊ ጥያቄ በጎረቤት ሀገራት በቅንነት ሊታይ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ህልውናዋን ለማስጠበቅ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ድረስ መሄድ የሚያስችላት ህጋዊ ማዕቀፍ በግልጽ እንዳለም ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የባህር በር እንዳትጠቀም ለመከልከል መብት ያለው የለም ያሉት ፕሮፌሰር ብሩክ፤ የባህር በር ያለው ሀገር የመተባበር ግዴታ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ በተከተለችው ሰላማዊ አካሄድ የባህር በር እንደሚያስፈልጋት ሀያላን ሀገራት ጭምር የተቀበሉት እውነት ሆኗል ብለዋል፡፡

ለኢትዮጵያ የባህር በር ተገቢነት ከአውሮፓ እስከ ባህረ ሰላጤው ሀገራት እውቅና መስጠት መጀመራቸው፤ የዲፕሎማሲያዊ ጥረት ፍሬ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም