ቀጥታ፡

ሰላምን በማጽናት ልማትን አጠናክሮ ለማስቀጠል በሚደረገው ጥረት የድርሻችንን እየተወጣን ነው

ደሴ/ደብረ ብርሃን ፤ ጥቅምት 20/2018(ኢዜአ)፡-ሰላምን በማጽናት ልማትን አጠናክሮ ለማስቀጠል በሚደረገው ጥረት የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን የደሴ እና የደብረ ብርሃን ከተማ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ገለጹ።

የደሴ ከተማ አስተዳደር "ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም" በሚል መሪ ሃሳብ ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር ዛሬ የውይይት መድረክ አካሂዷል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ ሄለን አሰፋ እንደገለጹት፣ የከተማዋን ሰላም አጠናክሮ ለማስቀጠል የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው  እንዲቀጥሉ ከመንግስት ጎን በመሰለፍ የድርሻቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።

በደሴ ከተማ ሰላም መስፈኑ የንግድ ሥራቸውን ያለምንም ችግር ለማከናወንና ቤተሰባቸውን ለመምራት እንዳስቻላቸውም ገልጸዋል። 

የከተማዋን ሰላም አጠናክሮ ለማስቀጠል በሚደረገው ሂደት በንቃት ከመሳተፈ ባለፈ ግብራቸውን በወቅቱ በመክፈል የከተማዋ ልማት እንዲፋጠን የድርሻቸውን መወጣታቸውን አስረድተዋል።


 

ሌላው የመድረኩ ተሳታፊ አቶ አህመድ ጀማል በበኩላቸው ለጤናማ የንግድ እንቅስቃሴ የሰላም ዋጋ የማይተካ ነው ብለዋል።

አሁን ላይ በአካባቢው ሰላም በመስፈኑ ምርትና ሸቀጣሸቀጥ ከሌላ አካባቢ ወደ ከተማዋ በማምጣት ሥራቸውን በአግባቡ ለማከናወን መቻላቸውን ተናግረዋል።

በአካባቢያቸው የሰፈነውን ሰላም በመጠበቅ የንግድ ሥራቸውንና ልማትን ለማፋጠን ቁርጠኛ መሆናቸውን የገለጹት አቶ አህመድ፣ የታጠቁ ኃይሎችም የመንግስትን የሰላም አማራጭ ተቀብለው ህብረተሰቡን መካስ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰይድ ካሳው በበኩላቸው የንግዱ ማህበረሰብ የደሴ ከተማና አካባቢውን ሰላም በዘላቂነት ለማስጠበቅ ከመንግስት ጋር በትብብር የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።


 

ወጣቶችን ስለ ሰላም ከማስተማር በተጨማሪ ገበያው እንዲረጋጋ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በተመሳሳይ ዜና በደብረ ብርሀን ከተማ የሚገኙ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት የከተማቸውን ሰላም በማጠናከር ልማት እንዲፋጠን ከመንግስት ጎን ሆነው የሚያደርጉትን ተሳትፎ እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።

የከተማዋ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት በዘላቂ ሰላምና በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ከከተማው መስተዳድር ኃላፊዎች ጋር ዛሬ መክረዋል።


 

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ንጉሴ ማሞ ሰላም ለሁለንተናዊ የልማት ሥራዎች ወሳኝ መሆኑን ገልጸው ለከተማቸው ሰላም መጠናከር የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

የንግድ ስራቸውን ለማከናወንም ሆነ ከልማት ሥራዎች ተጠቃሚ ለመሆን ሰላም ወሳኝ መሆኑን እና  በከተማቸው የሰፈነውን ሰላም ለማስቀጠል የህዝብ ትብብር አስፈላጊ ነው ብለዋል።

የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻልና የልማት ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ሰላምን ማጽናት አይነተኛ ሚና እንዳለው የገለጹት ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ ደግሞ አቶ ሳሙኤል አውግቸው ናቸው።

የሰላም እጦት ያለውን ተጽዕኖ እናውቀዋለን ያሉት ነዋሪው፣ ለሸቀጦች ዋጋ መናርና መጥፋት አንድ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል አመልክተዋል።


 

የንግድ ሥራቸውን በተረጋጋ ሁኔታ ለማከናወንና ሁለንተናዊ ልማት እንዲፋጠን በከተማቸው የሰፈነውን ሰላም ለማጽናት ተግተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ለእዚህም እንደ ንግዱ ማህበረሰብ አባል ከመንግስት ጎን በመቆም የበኩላቸውን  ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።

በተለይ ስለሰላም አስፈላጊነትና ሰርቶ ለመለወጥ ሰላም ያለውን ፋይዳ ለህብረተሰቡ የማስገንዘብ ስራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።    

መንግስት የጀመራቸው የልማት ስራዎች ዳር እንዲደርሱና በሰላም ወጥቶ ለመግባት ዘላቂ ሰላም ወሳኝ በመሆኑ ለሰላማቸው ቁርጠኛ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ ሼህ ኡስማን መሐመድ የተባሉ የከተማው ነዋሪ ናቸው።

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ምክትል ሀላፊ አቶ ደመረ ላቀው በበኩላቸው እንደገለጹት የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ከመንግስት ጎን ሆነው ለሰላም ያሳዩት ተነሳሽነት የሚበረታታ ነው።  


 

የዛሬው መድረክም የሰላም እጦት  በኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረውን ጫና ለማስገንዘብ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

ነጋዴው ሰርቶ ተጠቃሚ መሆን የሚችለው ሰላም በዘላቂነት ሲረጋገጥ መሆኑን ጠቅሰው፣ ህብረተሰቡ ለአካባቢው ሰላም መጠናከር ከመንግስት ጎን በመሆን የጀመረውን ተግባር እንዲያጠናክር አሳስበዋል።

በደሴ እና በደብረብርሀን ከተሞች በተካሄዱ የውይይት መድረኮች የንግዱ ማህበረሰብ፣ አመራሩና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም