ቀጥታ፡

የገጠር ኮሪደር ልማት መሰረታዊ የአኗኗር ለውጥ ያየንበት ነው -አርሶ አደሮች 

ወልቂጤ፤ ጥቅምት 20/2018(ኢዜአ)፡- የገጠር ኮሪደር ልማት መሰረታዊ የአኗኗር ለውጥ ያየንበት ነው ሲሉ በጉራጌ ዞን እኖር ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢንሼቲቭ የተጀመረው የገጠር ኮሪደር ልማት በስፋት ተግባራዊ እየሆነባቸው ካሉ አካባቢዎች መካከል የጉራጌ ዞን አንዱ ነው።


 

የገጠር ኮሪደር ልማቱ አርሶ አደሩ አኗኗሩን እንዲያዘምን ከማድረግ ባለፈ ለዓመታት ባህሉ አድርጎ የቆየውን ተፈጥሮን የመንከባከብ ልምድ ይበልጥ እንዲጎለብት ያስቻለ ነው።

የጉራጌ ማህበረሰብ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን ከጥንት ጀምሮ ሲያካሂድበት የቆየው "ጀፎረ" እየተጋረጠበት ያለው ሰው ሰራሽ አደጋን በመታደግ በኩልም የኮሪደር ልማቱ ትልቅ ሚና እየተወጣ ይገኛል።

በመሆኑም ዘንድሮ በዞኑ በሚገኙ 273 የገጠር ቀበሌዎች የገጠር ኮሪደር ልማት ተግባራዊ እየተደረገ ነው።

ልማቱ ከተተገበረባቸው አካባቢዎች አንዱ የሆነው እኖር ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ያጂቡ መሃመድ በገጠር ኮሪደር ልማት የሰውና የእንስሳት ማደሪያ ተለያይቶ በዘመናዊ መንገድ ለመኖር እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።


 

በጓሯቸው እንሰት፣ አትክልትና ፍራፍሬ ከማልማት በተጨማሪ ዝርያቸው የተሻሻሉ የዳልጋ ከብት እያረቡ መሆኑንም ገልጸዋል።

ሌላው የወረዳው ነዋሪ አርሶ አደር አብድልመናን አህመድም የገጠር ኮሪደር ልማት አካባቢውን ውብ ከማድረግ ባለፈ በጓሯቸው ዶሮ በማርባት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በእንሰት ልማት ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ነው የገለፁት።


 

በወረዳው የተጀመረው የገጠር ኮሪደር ልማት የነዋሪውን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባለፈ የመስህብ ስፍራ እየሆነ መምጣቱን የገለጹት ደግሞ የወረዳው ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ሀላፊ ወይዘሮ ጨዋነሽ ይልማ ናቸው።


 

የገጠር ኮሪደር ልማት በአካባቢው የአርሶ አደሩን ኑሮ ለማዘመን እያስቻለ መሆኑንም ተናግረዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በበኩላቸው ጀፎረ ከጉራጌ ማህበረሰብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ጋር የተቆራኘ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከገጠር ኮሪደር ልማት ጋር በማስተሳሰር የማህበረሰቡን ኑሮ የሚለውጥ እንዲሆን ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ማህበረሰቡ በአካባቢያዊ ልማት፣ በማህበራዊና መሰል ጉዳዮች ላይ በጋራ የሚመክርበትና አቅጣጫ የሚያስይዝበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ያሉትን እሴቶች ከማስተዋወቅ ባለፈ ተሻጋሪ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

መንደሮቹ ቀላል ወጪ በሚጠይቁና የአካባቢውን ግብዓቶች በመጠቀም የሚሰሩ መሆናቸውን ጠቁመው፣ በዚህም አርሶ አደሩ ጤናማ ሕይወት እንዲኖር ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

በተለይ ምቹና ጽዱ አካባቢን ከመፍጠር ባለፈ አርሶ አደሩ ጓሮውን በተለያዩ አትክልት፣ ፍራፍሬና እንሰት ስለሚያለማ ጤናውን ለመጠበቅ በሚያስችለው መልኩ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የገጠር ኮሪደር ልማትን በዞኑ ሁሉም የገጠር ቀበሌዎች ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ላጫ አመልክተዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም