ቀጥታ፡

የሉሲ እና ሰላም የመካከለኛው አውሮፓ ቆይታ የተሳካ ነበር 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 20/2018(ኢዜአ)፡-የሉሲ (ድንቅነሽ) እና ሰላም ቅሪተ አካላት ቅርሶች የመካከለኛው አውሮፓ ቼክ ሪፐብሊክ ቆይታ ኢትዮጵያን ይበልጥ በማስተዋወቅ ረገድ የተሳካ እንደነበር የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው (ረ/ፕ) ገለጹ።

በመካከለኛው አውሮፓ ፕራግ ብሔራዊ ሙዝየም ለህዝብ እይታ የቀረቡት የሉሲ (ድንቅነሽ) እና ሰላም የሰው ልጅ ቅድመ ቅሪተ አካላት በቼክ ሪፐብሊክ የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀው ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው (ረ/ፕ)፤ የሉሲና ሰላም ቅሬተ አካል ቅርሶችን የመካከለኛው አውሮፓ የጉዞ ቆይታ የተሳካ ለማድረግ እ.አ.አ. ከ2024 ጀምሮ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

በቅድመ ዝግጅት ወቅትም ዓለም አቀፍ የቅርስ ማጓጓዝ ሥነ-ስርዓቶችን በጠበቀ መንገድ ማከናወን የሚያስችሉ ስምምነቶችን በመፈጸም ወደ ቼክ ሪፐብሊክ እንዲያቀኑ መደረጉን ተናግረዋል።

ቅርሶቹን ለመጠበቅም ልዩ የማሸጊያ ሳጥን በማዘጋጀት ጭምር በኤግዚቢሽን መልክ ለዕይታ የሚቀርቡበትን ቦታ ደኅንነት የማረጋገጥ ተግባራት መከናወናቸውን አስረድተዋል።

በዚህም ቅርሶቹ የቀረቡበትን ቦታ የሙቀት መቆጣጣሪያ፣ የድኅንነት ማንቂያና የብርሃን መጠን አመችነት በማረጋገጥ በቼክ ሪፐብሊክ መዲና ፕራግ የሁለት ወራት ስኬታማ ቆይታ አድርገው መመለሳቸውን ገልጸዋል፡፡

በመካከለኛው አውሮፓ ፕራግ ብሔራዊ ሙዝየም የኤግዚቢሽን ቆይታም የሉሲ እና ሰላም ቅሬተ አካላትን ያገኙ ተመራማሪዎች ለጎብኝዎች ገለጻና ማብራሪያ መስጠታቸውን አስረድተዋል።  

የሉሲ (ድንቅነሽ) እና ሰላም ግዙፍ ቅርስነት በሚያሳይ መልኩ በቼክ ሪፐብሊክ ቆይታ የኢትዮጵያን ምድረ ቀደምትነት በጉልህ የተዘከረበት ነበር ብለዋል። 

በአውሮፓ ግዙፍ በሆነው የቼክ ሪፐብሊክ ፕራግ ብሔራዊ ሙዚየም በርካታ ቱሪስቶች የሉሲ (ድንቅነሽ) እና ሰላም ቅሪተ አካላትን የጎበኙበትን ዕድል እንደፈጠረ አስረድተዋል።

የሉሲ (ድንቅነሽ) እና ሰላም ቅሪተ አካል ቅርሶች የመካከለኛው አውሮፓ ቼክ ሪፐብሊክ ቆይታ ኢትዮጵያን በዓለም የማስተዋወቅ ዕድል መፍጠር እንደተቻለ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም