ቀጥታ፡

በክልሉ የግብርና ምርምር ማዕከላት ግብርናን በማዘመን ለዘርፉ ውጤታማነት ጉልህ አስተዋጽኦ አድርገዋል - ቢሮው

ወራቤ፤ ጥቅምት 20/2018(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የግብርና ምርምር ማዕከላት ግብርናን በማዘመን ለዘርፉ ውጤታማነት ጉልህ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የወራቤ ግብርና ምርምር ማዕከል ለስርዓተ ምግብ ማጠናከሪያ ፕሮግራም በዘር ብዜት፣ በምርምርና በቴክኖሎጂ ሽግግር ባከናወናቸው ተግባራት ላይ የመስክ ምልከታ ተካሂዷል።

የቢሮው ምክትልና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ ዓለምይርጋ ወልደስላሴ በዚህ ወቅት እንዳሉት በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የግብርና ምርምር ማዕከላት ተጨማሪ አቅም እየሆኑን ነው።

በግብርና ዘርፍ የስንዴ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በራስ አቅም የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ከተረጂነት ለመወጣት እየተደረገ ባለው ጥረት ተጨባጭ ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።

በሌማት ትሩፋት፣ በአረንጓዴ ዐሻራና በሌሎች የግብርና ሥራዎችም የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት በማሳደግ በኩል ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

ባለፈው ዓመት በክልሉ በበልግ፣ በመኸርና በበጋ መስኖ ልማት 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር ማሳ በማልማት 142 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱን ገልጸዋል።

ለዚህም የወራቤ ግብርና ምርምር ማዕከል በምርጥ ዘር ብዜት፣ የተሻሻሉና በምርምር የተደገፉ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅና በማሸጋገር ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን አስታውሰዋል።

በዚህ ዓመትም 159 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ግብ ተጥሎ ወደ ተግባር መገባቱን ነው ምክትል ቢሮ ኃላፊው የተናገሩት።

የክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጌታሁን ያዕቆብ(ዶ/ር) በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ የግብርና ልማት ሥራውን የሚያግዙ ተግባራት በማከናወን ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የሀገራዊና ክልላዊ ኢንሼቲቮች ትግበራን በምርምርና በቴክኖሎጂ እያገዘ እንደሚገኝም ነው የገለጹት።

የወራቤ ግብርና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ቀድራላ ዋበላ(ዶ/ር) እንዳሉት ማዕከሉ ግብርናን ማዘመን የሚያስችል የምርምር፣ የዘር ብዜትና ቴክኖሎጂን የማስተዋወቅ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

በዚህም የአካባቢን ስነ ምህዳር መሰረት በማድረግ የዘር ብዜት፣ የሰብል ጥበቃና እንስሳት ዝርያ ማሻሻልን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በመስክ ምልከታው የክልሉ ግብርና ቢሮ፣ የምርምር ኢንስቲትዩት ከፍተኛ አመራሮችና አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም