የትምህርት ጥራትን ለማሻሻልና ትውልድን ለማነጽ ተግባራዊ የተደረጉ ፕሮጀክቶች ስኬታማ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
የትምህርት ጥራትን ለማሻሻልና ትውልድን ለማነጽ ተግባራዊ የተደረጉ ፕሮጀክቶች ስኬታማ ናቸው
 
           አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 20/2018(ኢዜአ)፦ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻልና ትውልድን ለማነጽ ተግባራዊ የተደረጉ ፕሮጀክቶች በዘርፉ ስኬት እንዲመዘገብ እያደረጉ መሆኑን የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ገለፀ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ተግባራዊ የተደረገው የትምህርት ለትውልድ ፕሮጀክት የትምህርት ጥራትን ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት በስፋት እያገዘ መሆኑንም ተጠቁሟል፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከትናንት በስቲያ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ መንግስትና ሕዝብ በመተባበር ተግባራዊ ያደረጉት የትምህርት ለትውልድ ፕሮጀክት ስኬታማ ስራዎችን ለማከናወነ አስችሏል ብለዋል።
የፕሮጀክቱ አንዱ ዓላማ የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ መሆኑን አመልክተው፤ ከታችኛው የትምህርት እርከን ጀምሮ ትውልድን የሚገነቡና የሚያንጹ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ለመምህራን የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች በትምህርትና በፈተና አሰጣጥ ስርዓት ላይም ለውጥ ማስመዝገብ አስችሏል ነው ያሉት።
የተማሪዎች ምገባን በተመለከተም አስደናቂና ማሕበረሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ስራዎች መስራታቸውንም ነው ለምክር ቤቱ የገለጹት።
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት ዮሐንስ በንቲ(ዶ/ር ) ለኢዜአ እንዳሉት፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የትምህርት ጥራትን ለማምጣት የተከናወኑ ተግባራት ውጤት የተገኘባቸው ናቸው።
በዋናነት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ኢንሼቲቭ ተግባራዊ የተደረገው የትምህርት ለትውልድ ፕሮጀክት በዘርፉ የሚታይ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ገልፀዋል።
የአንደኛ ደረጃ ትምህርትን በማዳረስና በትምህርት ቤቶች ተግባራዊ የተደረገው የምገባ መርሃ ግብር ስኬት ከተመዘገበባቸው ዘርፎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።
እስካሁን ባለው ሒደት ፕሮጀክቱ ውጤታማ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ካሉት የትምህርት ተቋማት ብዛት አኳያ ፕሮጀክቱ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት።
ይህም ትውልዱን ለመገንባትና የትምህርት ዘርፉን በሚፈለገው ደረጃ መቀየር የሚያስችል መሆኑን በመጥቀስ።