ለኢትዮጵያ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ስኬት አቅም የሚሆን የሰው ሃይል እያፈራን ነው -ኢንስቲትዩቱ - ኢዜአ አማርኛ
ለኢትዮጵያ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ስኬት አቅም የሚሆን የሰው ሃይል እያፈራን ነው -ኢንስቲትዩቱ
 
           አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 20/2018(ኢዜአ)፡- ለኢትዮጵያ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ስኬት አቅም የሚሆን የሰው ሃይል እያፈራ እንደሚገኝ የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ገለጸ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ማብራሪያቸው የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ወደተሻለ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ ፕሮጀክቶቸ ዕውን መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያም ሀገርን ከጸጋዎቿ በማሰናሰል በብዝኅ የኢኮኖሚ ልማት ዕመርታዊ ስኬት ማስመዝገብ ያስቻሉ የአሰራር ሥርዓቶች መዘርጋታቸውን አስረድተዋል።
በማዕድን ዘርፍም የተፈጥሮ ጋዝ፣ ነዳጅና ሌሎች የማዕድን ጸጋዎችን በማልማት የኢትዮጵያን ዕድገት ወደተሻለ ማዕራፍ የሚያሸጋግሩ ግዙፍ ብሔራዊ ፕሮጀክቶች መጀመራቸውን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያን የግብርና ምርታማነት ዕመርታ ለማስቀጠል ከዳንጎቴ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጋር የተጀመረው የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካም የአርሶ አደሩን የግብዓት አቅርቦት ፍላጎት እንደሚፈታ አንስተዋል።
ኢትዮጵያን የአፍሪካ የአቬየሽን ኢንዱስትሪ ማዕከል የሚያደርጋት የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ፕሮጀክትን በተቀመጠለት የግንባታ ጊዜ ለማጠናቀቅ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ብሩክ ከድር (ዶ/ር)፤ በትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ንድፈ ሃሳብን ከተግባር በማዋሐድ ዕውቀትና ክህሎት የተላበሰ የሰው ሃይል እያፈሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ኢንስቲትዩቱ የሚያፈራው የሰው ሃይልም ለኢትዮጵያ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ግንባታ ስኬታማነት አዎንታዊ ሚና እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።
ለአብነትም በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት ከ400 በላይ ብቁ የብረታ ብረት ብየዳ ሙያተኞችን አሰልጥኖ በማሰማራት ገንቢ ሚና መወጣቱን አስረድተዋል።
በቀጣይም በዕውቀትና ክህሎት መር ትምህርትና ስልጠና በተለያዩ መርሃ ግብሮች ለኢትዮጵያ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ስኬት አቅም የሚሆን የሰው ሃይል የማፍራት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
አዳዲስ ስልጠና መርሃ ግብሮችን በመቅረጽ ጭምር በግብርና ማቀነባበር፣ ሥነ-ውበት፣ በቆዳና ሌጦ ተያያዥ የኢንዱስትሪ መስኮችም ብቃት ያላቸው ሙያተኞችን በማፍራት ላይ እንደሚገኝ አንስተዋል።
በፕላስቲክ ቴክኖሎጂ፣ በተሽከርካሪ ጥገና ዘርፎችም የትምህርትና ስልጠና መርሃ ግብር በመስጠት የዘርፉን ዕድገት የሚደግፍ የሰው ሃብት እንደሚያፈሩ ገልጸዋል።
በመጨረሻም በቅርቡ የተጀመሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች አስፈላጊ የሆኑ ሙያተኞችን ማፍራት የኢንስቲትዩቱ ቀዳሚ ተግባር መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢንስቲትዩቱ በዚህ ላይ በትኩረት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።