ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በታላቅ የልማት ሽግግር ላይ ትገኛለች - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 20/2018(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ በታላቅ የልማት ሽግግር ላይ ለመሆኗ የኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ምስክር ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምሥራቅ ሸዋ ዞን የግብርና ሥራዎችን ጎብኝተዋል።

ከጉብኝታቸው በኋላ በሰጡት ማብራሪያም፤ በስምጥ ሸለቆው ከባቢ አርሶ አደሮች ራዕይ ተላብሰው እየሠሩ፣ ሜካናይዜሽን እየተስፋፋ፣ የገበያ ትስስሩ እየሰመረ መንግሥትም ብቁ አመራር እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የዚህ ሁሉ ትጋት እና ቅንጅት መዳረሻው ያለምነው ያቀድነው የኢትዮጵያ ብልጽግና ነው ብለዋል።

በርካታ ኮምባይነር ተሰማርቶ የደረሰው ስንዴ ሰብል እየተሰበሰበ፤ ጎን ለጎንም ለበጋ ስንዴ ልማት ሥራ እየተዘጋጀ መሆኑን ማየታቸውን ተናግረዋል።

አካባቢው ዝናብ አጠርና ስምጥ ሸለቆ የሚያልፍበት በመሆኑ በሴፍቲኔት የሚረዳ እንደነበር ጠቁመው አሁን ግን የከርሰ ምድር ውኃንና በአካባቢው የሚያልፈውን አዋሽ በመጠቀም ዘርፈ-ብዙ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።

ይህም አርሶ አደራችን ምን ያህል ከተረጂነት ወደ አምራችነት እየተቀየረ እንደሆነ ማሳያ ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል ከስንዴ ልማቱ ባሻገር ሙዝና ፓፓያ በክላስተር እየለማ መሆኑን መመልከታቸውንም ተናግረዋል።


 

አሁን አርሶ አደሩ ስንዴን ጨምሮ አትክልትና ፍራፍሬ በክላስተር በስፋት እያመረተ ነው፤ ይህም የኢትዮጵያን የማንሠራራት እና የብልጽግና አይቀሬነት የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

በሀገር በቀል ሪፎርሙ ከመረጥናቸው አምስት ዘርፎች ውስጥ ግብርና አንዱ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በግብርና የምንሠራው ሥራ ለአምራች ኢንዱስትሪው ትልቅ ግብዓት ነው ብለዋል።

ይህን እያጠናከርን ስንሄድም ከተረጂነት የመውጣት ዕድላችን በቅርብ ጊዜ እንደሚረጋገጥ ያሳያል ነው ያሉት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም