ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና በሉአላዊነቷ ላይ አቋማችን የማይናወጥ ነው -የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች

ሚዛን አማን ፤ጥቅምት 20/2018 (ኢዜአ)፡-የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ቢኖረንም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና በሉአላዊነቷ ላይ ግን አቋማችን የማይናወጥና አንድ ነው ሲሉ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተናገሩ።

በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ እየጎለበተ እንዲሄድ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል።

በዚህም የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በፌዴራልና በክልሎች የጋራ ምክር ቤት በመመስረት የሀሳብ ክርክሮችን በማድረግ በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ እየሰሩ ይገኛሉ።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም፣ የሀገር ልማትና የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ዙሪያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ኢዜአ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን አነጋግሯል።

የፓርቲዎቹ አመራሮችም የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ቢኖርንም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና በሉአላዊነቷ ላይ ግን አቋማችን አንድና ሊናወጥ የማይችል ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የባህር በር ማጣት የሚያስቆጭና መልሳ ማግኘት እንዳለባት የጸና እምነት እንዳላቸው አንስተው በዚህ ረገድ መንግስት የጀመረውን እንቅስቃሴና ያለውን አቋም እናደንቃለን ብለዋል።

የባህር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያና ህዝቦቿ የህልውና ጉዳይ ተደርጎ መያዙ ሁላችንንም የሚያስማማ በመሆኑ በሁሉም ረገድ የመንግስትን አቋም እንደግፋለን ሲሉም አረጋግጠዋል። 

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ እና የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ፓርቲ ተወካይ ጎዳና ሙንኤ፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ያጣችበት መንገድ ምክንያቱ የማይታወቅ፣ የሁልጊዜም ቁጭትና የታሪክ ስብራት ጭምር መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና መንግስታቸው የቀይ ባህር ጉዳይ ህጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልክዓ ምድራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ መሆኑን በፅኑ አምኖ ምላሽ እንዲያገኝ የጀመረውን ጥረት እናደንቃለን፤ እንደግፋለንም ብለዋል።

የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ቢኖርንም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም፣ በሉአላዊነቷ እና በተለይም በባህር በር ጉዳይ ላይ አቋማችን ሊናወጥ አይችልም ሲሉም አረጋግጠዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ አባልና ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) አቶ ሰሎሞን መኮንን፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ማጣት ብሔራዊ ጥቅሟን በእጅጉ የጎዳ፣ የሚያስቆጭና የታሪክ ተወቃሽ የሚያደርግ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም ምክንያት እስካሁን ኢትዮጵያ ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለች መሆኑን ተናግረው መንግስት የባህር በር ሊኖራት የግድ ይላል ብሎ አቋም መያዙ ተገቢና ሁላችንም የምንደግፈው አጀንዳ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የባህር በር ማጣት በፍፁም የቀባይነት የሌለው መሆኑን አስታውሰው ከቀይ ባህር በቅርብ እርቀት ላይ ሆና የተቆለፈባት ሀገር ሆና መዝለቅ የለባትም ሲሉ አፅኖት ሰጥተዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ በታሪክም፣ በህግም ይሁን በመልካአ ምድር የባህር በር የማግኘት መብት አላት ለዚህም ስኬት በጋራ እንቆማለን ሲሉ አረጋግጠዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም