በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላምን ለማጽናትና ልማትን ለማስቀጠል በሚደረገው ጥረት የድርሻችንን እንወጣለን - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላምን ለማጽናትና ልማትን ለማስቀጠል በሚደረገው ጥረት የድርሻችንን እንወጣለን
ደብረ ብርሃን/ ገንዳ ውሃ/ደሴ፤ ጥቅምት 19/2018(ኢዜአ)፡ - በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላምን ለማጽናትና ልማትን ለማስቀጠል በሚደረገው ጥረት የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ በክልሉ የተለያዩ ከተሞች የሚኖሩ የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተናገሩ።
በአማራ ክልል በደብረ ብርሃን፣ ገንዳ ውሃ እና ደሴ ከተሞች የሚገኙ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።
ከደብረ ብርሃን ከተማ የውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ቀሲስ እሸቱ ተክለዮሃንስ እና አቶ ሁሴን ይመር፤ በከተማዋ አሁን ላለው ሰላምና ልማት የነዋሪውና የጸጥታ ሃይሉ የተቀናጀ ጥረት ውጤት መሆኑን አንስተዋል።
የሰላም ጉዳይ ለማንም የማንተወው የጋራ አጅንዳችን ሆኖ ቀጥሏል ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ ሰላምን ለማጽናትና ልማትን ለማስቀጠል በሚደረገው ጥረት የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ አረጋግጠዋል።
የከተማዋ የሀገር ሽማግሌ የሆኑት አቶ ለገሰ ሽፈራው፣ በበኩላቸው የሰላም ጥረታችን እና የልማት ትጋታችን ወደ ኋላ የማይመለስ ነው ብለዋል።
በመሆኑም ለከተማዋና አካባቢው ዘላቂ ሰላም መረጋገጥና ለተጀመሩ የልማት ስራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው በተለይም የሀገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶችና አጠቃላይ ማህበረሰቡ ጠንካራ ተሳትፎና ትብብር በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።
የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ሀላፊ አቶ ዳንኤል እሸቴ፤ ለማንኛውም ችግር መፍትሄዊ ሰላማዊ ውይይት መሆኑን በማመን መንግስት በዚህ ረገድ ብዙ እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።
በዚህ ጥረት ውስጥ በተለይም የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው የሰላም ጥረቶችንና የልማት አቅሞችን መጠቀማችን ቀጣይነት ይኖረዋል ብለዋል።
በተያያዘ ዜና በምዕራብ ጎንደር ዞን የመተማ ወረዳ የሃይማኖት አባት መላዕከ ኃይል ፍሬው ዘመነ፤ በበኩላቸው የአካባቢያቸውን ሰላም በማስፈን የተጀመረው ልማት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከመቼውም ግዜ በላይ ሀላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
ሌላኛው የመድረኩ ተሳታፊ የሀይማኖት አባትና የሀገር ሽማግሌ ሼህ አደም ሱሌማን፤ የሀገሪቱን እድገት የማይፈልጉ የውጭ ጠላቶች እና የውስጥ ባንዳዎች ሰላምን ለማናጋትና ልማትን ለማደናቀፍ እየጣሩ ስለመሆኑ እንገነዘባለን ብለዋል።
በመሆኑም በሁሉም አካባቢዎች ለሰላማችን መረጋገጥና እና ለልማታችን ቀጣይነት በጋራ ቆመን መስራት ይገባናል ሲሉ አስገንዝበዋል።
በደሴ ከተማ በተካሄደው ተመሳሳይ መድረክ ላይ የተገኙት መላከ ብርሃን ቆሞስ አባ ተስፋሚካኤል፣ ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት በመሆኑ ለሰላም ግንባታ የምንሰስተው ነገር ሊኖር አይገባም ብለዋል።
ከግጭትና ጦርነት ጉዳት እንጅ ጥቅም አለመኖሩን በተግባር አይተናል ያሉት አባ ተስፋሚካኤል ሰላማችንን በመጠበቅ የተጀመሩ ሰፋፊ የልማት ስራዎችን ከዳር ማድረስ ይጠበቅብናል ሲሉ አስገንዝበዋል።
ሌላኛው የሐይማኖት አባት ሼህ ሀሽም መሀመድ፣ ሰላም ወሳኝ በመሆኑ ለሰላም መስፈን ከመንግስት ጋር በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰይድ ካሳው፤ የከተማውን ሰላም ከሕብረተሰቡና ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር አስተማማኝ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
በከተሞቹ በተካሄደው ውይይት ላይ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።