ቀጥታ፡

መንግስት በማህበራዊ ዘርፎች ያደረጋቸው ማሻሻያዎች የዜጎችን ተጠቃሚነት እያረጋገጡ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 19/2018(ኢዜአ)፦ የትምህርት እና የጤና ተደራሽነትንና ጥራትን ለማስጠበቅ የተወሰዱ እርምጃዎች የዜጎችን ተጠቃሚነት እያረጋገጡ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት ትላንት መካሔዱ ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ሰፊ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚህም የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በተሰሩ ስራዎች 63 ሚሊዮን ዜጎች የጤና መድህን ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን ተናግረዋል።

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ለመምህራን የተለያዩ ስልጠናዎችን ከመስጠት ባሻገር በመማር ማስተማርና በፈተና አሰጣጥ ላይ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል የአሰራር ተግባራዊ መደረጉን ጠቅሰዋል።

በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ከ43 ሚሊየን በላይ የሁለተኛ ደረጃ የመማሪያ መጻሕፍት መከፋፈላቸውን አስታውሰው፤ ለአንድ ተማሪ አንደ መጽሃፍ ተደራሽ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ይህም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ከተሰሩ ስራዎች መካከል ተጠቃሽ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማብራሪያ ተከትሎ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች እንደገለጹት፤ የትምህርት፣ የጤና ተደራሽነትና ጥራትን ለማስጠበቅ የተከናወኑ ስራዎች የዜጎችን ተጠቃሚነት እያረጋገጡ ይገኛሉ።

አቶ ሃሰን በየነ የተባሉ ነዋሪ እንደገለጹት፤ መንግስት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና ተደራሽነቱን ለማስፋት የወሰደው ማሻሻያ የሚበረታታ ነው።

በዘርፉ የተከናወኑ ተግባራት የመንግስትን ቁርጠኝነት በተግባር ያረጋገጡ መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይ ለሚከናወኑ ስራዎች ሁሉም የሚጠበቅበትን ሃላፊነት ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

አቶ ይትባረክ ዮሃንስ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው፤ መንግስት የትምህርት ስርዓቱን ለማሻሻል የጀመረው ጥረት ውጤት እያመጣ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግስት የሚያወጣቸውን የአሰራር ስርዓቶች እስከታችኛው መዋቅር በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል።

በጤናው ዘርፍ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን የገለጹት አቶ ሙሉጌታ ጥበቡ፤ በተለይም በጤና መድህን በመታገዝ ዜጎች ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን አንስተዋል።

በተጨማሪም በሆስፒታል ደረጃ የሚሰጡ ህክምናዎች በጤና ጣቢያ እንዲሰጡ መደረጉ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ማረጋገጥ ማስቻላቸውን ጠቅሰዋል።

አቶ ሰላም ጀማል የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ መንግስት የዜጎችን ዘላቂ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ በርካታ የልማት ስራዎች አከናውኗል።

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት በእውቀት የዳበረ ትውልድ መፍጠር የሚያስችሉ ናቸውም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም