ቀጥታ፡

የእጽዋትና እንስሳት ጤና አጠባበቅ መስፈርቶችን ማሟላት ለወጪ ንግድ መሳለጥ ትልቅ ትርጉም አለው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 19/2018(ኢዜአ)፦ የእጽዋትና እንስሳት ጤና አጠባበቅ መስፈርቶችን ማሟላት ለወጪ ንግድ መሳለጥ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ተመላከተ።

የኢትዮጵያ የግብርና ባለሥልጣን የግብርና ምርቶችን ወደ ውጭ ለመላክና የጥራት ደረጃን ለማሻሻል የሚረዱ ሁለት ፕሮግራሞችን በይፋ አስጀምሯል። 


 

ሁለተኛው ቀጣናዊ የእጽዋትና እንስሳት ጤና አጠባበቅ(SPS - Sanitary and Phytosanitary Measures) ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል። 

ለሁለት ቀናት የሚካሄደው ይህ ጉባዔ በኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣንና በኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራቾችና ላኪዎች ማኅበር በጋራ የተዘጋጀ ነው።

የኢትዮጵያ የግብርና ባለሥልጣን በጉባዔው ላይ የግብርና ምርቶችን ወደ ውጭ ለመላክና የጥራት ደረጃ ለማሻሻል የሚረዱ ኢ-ፋይቶ (ePhyto) እና ማኅበር (MAHEBER)  የተባሉ ሁለት ፕሮግራሞችን በይፋ አስጀምሯል።

ኢ-ፋይቶ የእጽዋት ጤና የምስክር ወረቀት በኤሌክትሮኒክስ የሚሰጥበት ሥርዓት ሲሆን፤ ሥርዓቱ የግብርና ምርቶችን ወደ ውጭ የመላክ ሂደቱን ፈጣንና ደህንነቱ የተጠበቀ የሚያደርግ መሆኑ ተገልጿል።

ማኅበር የተባለው ፕሮግራም ደግሞ የሆርቲካልቸር ዘርፉን ተወዳዳሪነት፣ የጥራት ደረጃና ዘላቂነት ለማሳደግ ያለመ የልማት ፕሮግራም መሆኑ ተገልጿል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለሰ መኮንን(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ የእጽዋትና እንስሳት ጤና አጠባበቅ(SPS) መስፈርቶችን ማሟላት ለኢትዮጵያም ሆነ ለአፍሪካ የወጪ ንግድ መሳለጥ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ገልጸዋል።

የእንስሳት እና እጽዋት ጤና አጠባበቅ ዓለም አቀፍ ንግድን፣ ደህንነትና ጥራትን የሚያረጋግጥ ሥርዓት መሆኑን ጠቁመው፤  ለዓለም አቀፍ ንግድና ለባዮሴኩሪቲ መሠረት እንደሆነ ገልጸዋል።

የእንስሳት እና እጽዋት ጤና አጠባበቅ መስፈርቶችን ማሟላት የገበያ ተደራሽነትን ከማረጋገጥ፣ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ከማሳደግ እንዲሁም የምርቶችን ጥራትና ደህንነት ከማረጋገጥ አኳያ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው ብለዋል። 

ሚኒስትር ዴኤታው የኢ-ፋይቶ እና የማኅበር ፕሮግራሞች መጀመር የኢትዮጵያን ግብርና ዘርፍ ተወዳዳሪነትና ዘላቂነት ለማረጋገጥ ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑንም አረጋግጠዋል።


 

የኢትዮጵያ የግብርና ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ድሪባ ኩማ በበኩላቸው፤ የኢ-ፋይቶ ሥርዓት በወረቀት ላይ የተመሠረተውን አሠራር በዲጂታል ቴክኖሎጂ የሚተካ እንዲሁም የወጪ ንግድ ቀልጣፋ፣ ግልጽና አስተማማኝ እንዲሆን በእጅጉ እንደሚረዳ ገልጸዋል። 

አያይዘውም ኢ-ፋይቶ የላኪዎችን የወጪ ገበያ ተወዳዳሪነት የሚጨምር እና የሚገጥሟቸውን የጊዜና የሰነድ አያያዝ ችግሮች የሚፈታ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራችና ላኪዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዘላለም መሰለ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች መዳረሻ ሀገራት አዳዲስ ሕጎች ማውጣት መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡  


 

የኢ-ፋይቶ ሥርዓት መዘመን የወጭ ንግዱን ይበልጥ ተወዳዳሪ እንደሚያደርገውም ነው የተናገሩት። 

ባለሥልጣኑ የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ያላቸውን ተወዳዳሪነት ለማጠናከር የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም