ቀጥታ፡

መንግስት በተደጋጋሚ የሚያቀርበው የሰላም አማራጭ ለዘላቂ ሰላምና እድገት መረጋገጥ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 19/2018(ኢዜአ)፦ መንግስት በተደጋጋሚ የሚያቀርበው የሰላም አማራጭ የሚደነቅና ለዘላቂ ሰላምና እድገት መረጋገጥ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

ጥያቄ አለን የሚሉ ቡድኖች በመንግስት የቀረበውን የሰላም አማራጭ በመቀበል ልዩነታቸውን በውይይት ለመፍታት መዘጋጀት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት ትናንት መካሄዱ ይታወቃል።

በዚሁ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

መንግሥት ወደ ሰላም ከሚመጣ የትኛውም ኃይል ጋር አብሮ ለመስራት ሁልጊዜም ዝግጁ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በድጋሚ አረጋግጠዋል።

በዚህም የሰላምና የጸጥታ ችግር ለሚስተዋልባቸው አንዳንድ አካባቢዎች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት መንግሥት ለሰላም አማራጭ ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የምክር ቤቱ አባላት ላነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ መንግስት ሰላምን ለማጽናት ያለውን ቁርጠኝነት ተገንዝበናል ብለዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት የመዲናዋ ነዋሪዎች መካከል ፈቃዱ ጳውሎስ፤ ሰላም የሀገርን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማስቀጠል ሁነኛ መሳሪያ መሆኑን ገልጸዋል።

ከሰላማዊ አማራጭ ውጪ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የሀገርን ልማትና ዕድገት በማደናቀፍ ዜጎችን ለእንግልት የሚዳርጉ መሆናቸውንም አንስተዋል።

በዚህም የመንግስትን የሰላም ጥሪ ያልተቀበሉ ቡድኖች የሰላም አማራጭን በመቀበል አሉኝ የሚሏቸውን ጥያቄዎች በሰለጠነ መንገድ በውይይት መፍታት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።

የሰላምን መንገድ በመምረጥ ህዝብና ሀገራቸውን በመካስ የሀገር ዕድገት አቅም እንዲሆኑም ነው የተናገሩት።

በቀጣይም ለሀገር ሰላምና አንድነት በጋራ በመቆም የኢትዮጵያን ከፍታና የህዝብን ተጠቃሚነት በሚያስቀጥሉ የልማት ዘርፎች በትብብር መስራት አለብን ብለዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ሀቢብ አህመድ፤ ሰላም ለዜጎች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ መሰረት መሆኑን ጠቅሰው ሁሉም ዜጋ የሰላም አርበኛ በመሆን ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ዕድገት በጋራ መቆም እንዳለበት ገልጸዋል።

ሀገራዊ የሰላም ግንባታ የሁሉንም ዜጋ ቀና ትብብር የሚጠይቅ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አያሌው ዘለቀ ጠቅሰዋል።

ወይዘሮ ሸዋንብረት ማሞ በበኩላቸው፤ የሰላም አማራጭን ያልተከተሉ ወገኖች ምክክርን ሊያስቀድሙ ይገባል ብለዋል።

የመንግስት የሰላም አማራጭ የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት ያስችላል ያሉት ወይዘሮ ሸዋንብረት፤ በጫካ የሚንቀሳቀሱ ወገኖችም የመንግስትን የሰላም ጥሪ እንዲቀበሉ መክረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም