በወላይታ ሶዶ ከተማ በህብረተሰቡ ተሳትፎ የወባ በሽታን ቀድሞ ለመከላከል እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በወላይታ ሶዶ ከተማ በህብረተሰቡ ተሳትፎ የወባ በሽታን ቀድሞ ለመከላከል እየተሰራ ነው
ወላይታ ሶዶ፤ ጥቅምት 19/2018(ኢዜአ)፡-በወላይታ ሶዶ ከተማ በህብረተሰቡ ተሳትፎ የወባ በሽታ መከላከል ዘዴዎችን በአግባቡ በመተግበር የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ጤና መምሪያ አስታወቀ።
በከተማ አስተዳደሩ ሁሉም ቀበሌዎች የወባ በሽታ ሥርጭትን ለመግታት በህብረተሰቡ ተሳትፎ የአካባቢ ቅኝትና ቁጥጥር ሥራ እየተከናወነ መሆኑም ተመላክቷል።
ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በክልሉ የወባ በሽታ ስርጭት በስፋት ከሚታይባቸው አካባቢዎች ወላይታ፣ ጋሞ፣ ደቡብ ኦሞ፣ አሪ እና ጎፋ ዞኖች እንዲሁም ወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር ይጠቀሳሉ።
የክረምት መውጣትን ተከትሎ የወባ በሽታ ስርጭት ከተስተዋለባቸው አካባቢዎች የወላይታ ሶዶ ከተማ አንዱ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ፍሬው ዳዊት ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም በህብረተሰቡ ተሳትፎ የወባ መከላከልና መቆጣጠር ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ከመስከረም እስከ ታህሳስ ወር የወባ በሽታ ስርጭት የሚበዛበት ወቅት መሆኑን ያስታወሱት አቶ ፍሬው፣ የዝናብ መቆራረጥና ያቆረ ውሃ ለወባ ትንኝ መራቢያ አመቺ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም በከተማ አስተዳደሩ በህብረተሰቡ ተሳትፎ ከቤትና ከግቢ ጀምሮ ውሃ ያቆሩና ለወባ ትንኝ መራቢያ አመቺ የሆኑ ቦታዎችን የማጽዳትና የማዳፈን ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የቤት ለቤት ኬሚካል እርጭት ሥራ እንዲሁም የወባ በሽታ ምልክት የታየባቸውን ሰዎች ፈጥኖ የማከም ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህ ረገድ አስካሁን በተከናወኑ ሥራዎች የተሻለ ውጤት መምጣቱን አቶ ፍሬው ጠቁመው ህብረተሰቡ፣ የጤና ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት በወባ በሽታ መከላከል ላይ ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ አስገንዝበዋል።
"የወባ ስርጭትን ለመከላከል ከጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው" ያሉት የሶዶ ከተማ ጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ ተፈሪ ሀዳሮ በበኩላቸው በአካባቢ ንጽህና ላይ የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።
በቅንጅት በተሰሩ ሥራዎች የወባ በሽታን የስርጭት መጠን ለመቀነስ መቻሉን ጠቁመው፣ በሽታውን ቀድሞ የመከላከሉ ሥራ በንቅናቄ እየተመራ መሆኑን ተናግረዋል።
የጤና ጣቢያው ሁሉም ባለሙያዎች ሙሉ ጊዜያቸውን ለሥራ እያዋሉ መሆኑን የተናገሩት አቶ ተፈሪ፣ በዚህም የወባ ምልክት የታየባቸው ሰዎች ሲመጡ ፈጣን የሕክምና አገልግሎት እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የተለያዩ የወባ በሽታ መከላከያ ዜዴዎችን በአግባቡ በመተግበር ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ከበሽታው ለመከላከል እየተጉ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ አቶ ዮናስ ታንቱ የተባሉ የከተማው ነዋሪ ናቸው።
ሌላኛው የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ አማረች ወታንጎ በበኩላቸው በአካባቢያቸው የወባ ትንኝ መራቢያ እንዳይኖር መኖሪያ ግቢያቸውን የማጽዳትና ያቆሩ ውሃዎችን የማፋሰስ ሥራ ማከናወናቸውን ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ከጤና ባለሙያዎች ባገኙት ትምህርት መሰረት አጎበር በአግባቡ በመጠቀም ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ከወባ በሽታ እየተከላከሉ መሆናቸውን አስረድተዋል።
እንደሀገር ወባ የህብረተሰቡ የጤና ስጋት ወደማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት የተለያዩ የወባ መከላከያ ስልቶች ተነድፈው ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑ የሚታወቅ ነው።