መንግስት በባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ የያዘው አቋም ህዝባዊ መሰረት ያለው ነው - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት በባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ የያዘው አቋም ህዝባዊ መሰረት ያለው ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 19/2018(ኢዜአ)፦ መንግስት በባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ የያዘው አቋም ህዝባዊ መሰረት ያለውና የሀገር ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑ ተመላከተ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ትናንት ተካሂዷል።
በዚሁ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይም ስለ ባህር በር ያነሷቸውን ሐሳቦች አስመልክቶ ኢዜአ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን አነጋግሯል፡፡
የመዲናዋ ነዋሪ ገዛኽኝ አበበ እንዳሉት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በምክር ቤት ውሏቸው የባህር በርን በተመለከተ ያነሷቸው ሃሳቦች የህዝብ የልብ ትርታ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ የባህር በር ያጣችበት መንገድ ሁሌም እንደሚቆጫቸው ተናግረው፤ ወደብ በማጣታችን ጉሮሯችን ተዘግቷል ብለዋል፡፡
መንግስት የባህር በር ለማግኘት በሚያደርገው ማንኛውም እንቅስቃሴ ህብረተሰቡ በጋራ እንደሚቆም አመላክተዋል፡፡
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አብዱ ዳውድ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የባህር በር አልባ የሆነችበት አግባብ ህጋዊ እና ታሪካዊ መሰረት የሌለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
መንግስት የባህር በር ለማግኘት የያዘው አቋም ህዝባዊ መሰረት ያለው መሆኑን ተናግረው፤ ኢትዮጵያ እውነት ስላላት ታሳካዋለች ብለዋል፡፡
ሌላው አስተያየት ሰጪ ቦጋለ ድሮ በበኩላቸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የባህር በርን በተመለከተ ለምክር ቤቱ ያቀረቧቸው ሃሳቦች ወቅታዊና ተገቢነት ያላቸው መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡
ከህዝብ ቁጥር መጨመር እና ከኢኮኖሚ እድገት ጋር ተያይዞ ለኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት ውዴታ ሳይሆን ግዴታ ጭምር ነው ብለዋል፡፡
ለዚህም ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን መቆም እንዳለበት ነው የተናገሩት፡፡
የባህር በር ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ነው፤ በመሆኑም የባህር በር ለማግኘት በሚደረገው ጥረት ህዝብ ከመንግስት ጎን ነው ያሉት ደግሞ ኢብራሔም መሐመድ ነው፡፡