ቀጥታ፡

በምዕራብ ሐረርጌ ዞን የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን ለማሳካት ከ750 በላይ የውሀ መሳቢያ ሞተሮች ለአርሶ አደሮች ተከፋፈሉ

ጭሮ፤ ጥቅምት 19/2018(ኢዜአ)፡- በምዕራብ ሐረርጌ ዞን  የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን  ለማሳካት ከ750 በላይ የውሀ መሳቢያ ሞተሮች ለአርሶ አደሮች መከፋፈላቸውን  የዞኑ እርሻ እና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ፅህፈት ቤት አስታወቀ።

በፅህፈት ቤቱ የመስኖ አጠቃቀም እና ህዝብ ተሳትፎ ቡድን መሪ አቶ አብደላ ሙዘሚል ለኢዜአ እንደገለፁት የውሀ መሳቢያ ሞተሮቹ የተሰራጩት በዞኑ 15 ወረዳዎች በልማቱ  ለተሰማሩ በ668 ማህበራት ለተደራጁ  አርሶ አደሮች ነው።

በዓመቱ በሁለት ዙር በሚካሄደው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት  ሁለት ሺህ  የውሀ መሳቢያ ሞተሮች ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

በዓመቱ የሚሰራጨው የውሀ መሳቢያ ሞተር ከባለፈው ዓመት በእጥፍ እንደሚበልጥ ገልፀዋል።

በአካባቢው ተስማሚ መሬት  መኖሩና  አርሶ አደሩ በየአመቱ ከልማቱ እያገኘ ያለው ምርት መጨመር ምርትና ምርታማነት  እንዲያድግ  ማገዙን  አመልክተዋል።

በዞኑ በዓመቱ ከ81ሺ 200 ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ  ሰንዴ  ለማልማት ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን  የገለጹት ደግሞ በፅህፈት ቤቱ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት አስተባባሪ አቶ ሀቢብ አብዱልከሪም  ናቸው። 

ይህም  የዚህ ዓመት በበጋ መስኖ ስንዴ የሚለማው መሬት ካለፈው ዓመት ከ1ሺ 200 ሄክታር በላይ ብልጫ እንዳለው ነው ያመለከቱት።

እስካሁንም 10 ሺህ ሄክታር የሚሆን መሬት ታርሶ ለዘር መዘጋጀቱን ገልፀው ከዚህ ውስጥ 1 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ በዘር መሸፈኑን አብራርተዋል።

በዚህ አመት ከሚለማው መሬት ከሶስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

በዞኑ ባለፈው ዓመት 80 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ መሸፈኑንና ከ2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ገልፀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም