የኢትዮጵያ የባህር በር መሻት ከፍትሃዊ ተጠቃሚነትም ባለፈ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ምላሽ ሊሰጠው የሚገባ መሰረታዊ ጥያቄ ነው-ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህር በር መሻት ከፍትሃዊ ተጠቃሚነትም ባለፈ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ምላሽ ሊሰጠው የሚገባ መሰረታዊ ጥያቄ ነው-ምሁራን
ሮቤ፤ጥቅምት 19/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የባህር በር መሻት ከፍትሃዊ ተጠቃሚነትም ባለፈ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ምላሽ ሊሰጠው የሚገባ መሰረታዊ ጥያቄ መሆኑን የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ሙሁራን ገለጹ።
ምሁራኑ መንግሥት በዚህ ረገድ የያዘው አቋም ወቅታዊና ሊደገፍ የሚገባ የትውልድን የብዙ አመታት ጥያቄን የሚመልስ መሆኑንም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ከተነሱላቸው ጥያቄዎች መካከል የባህር በር ጉዳይ አንዱና ዋነኛው ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያም የቀይ ባህር ጉዳይ ህጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልከዓ ምድራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ ሲሆን የኢትዮጵያ የባህር በር መሻት የህልውና ጉዳይ መሆኑንም አጽኖት ሰጥተዋል።
በመሆኑም በሰላማዊ መንገድ ጥያቄው መቅረቡን አንስተው፤ የኢትዮጵያን የቀይ ባህር የማጣት ውሳኔ ማን ወሰነ ብለን ስንፈልግ ተቋማት ያልገቡበት መሆኑንና ኢትዮጵያ የባሀር በር አልባ የሆነችበት ምክንያትም እስካሁን ግልጽ አለመሆኑን አስረድተዋል።
ጉዳዩን በማስመልከት ኢዜአ ያነጋገራቸው የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን፤ የኢትዮጵያ የባህር በር መሻት ከፍትሃዊ ተጠቃሚነትም ባለፈ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ምላሽ ሊሰጠው የሚገባ መሰረታዊ ጥያቄ ነው ብለዋል።
ከዩኒቨርሲው ምሁራን መካከል የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት መምህርና ተመራማሪ ጉተማ አደም (ረዳት ፕሮፌሰር)፥ ኢትዮጵያ የባህር በር ያጣችበት ሁኔታ ህጋዊ መሰረት የሌለውና የሚያስቆጭ መሆኑን አንስተዋል።
ሀገሪቷ የባህር በር በማጣቷ ለተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ጫና መዳረጓን ጠቅሰው፥ መንግሥት በዚህ ረገድ የያዘው አቋም ወቅታዊና በዜጎች ሊደገፍ የሚገባ የህልውና ጥያቄ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የባህር በር ያጣችበት ሁኔታ በሞራልም ሆነ በህግ አግባብ ተቀባይነት የሌለውና ኢ-ፍትሃዊ አሰራር መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላው በዩኒቨርሲቲው የፍልስፍና ትምህርት መምህርና ተመራማሪ አቶ ካሚል ከድር ናቸው።
ኢትዮጵያ የባህር በር ከሌላቸው የዓለም ሀገራት ባላት ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ብዛትና ለባህር ባላት ቅርበት ልዩ እንደሚያደርጋትም አመልክተዋል።
መንግስት በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት፣ በሰጥቶ መቀበልና በድርድር የባህር በሩን ለማግኘት የጀመራቸው እንቅስቃሴዎች ሊደገፉ የሚገባና ፍትሃዊ ጥያቄ መሆኑንም አስረድተዋል።
መንግስት ያነሳው የባህር በር ጉዳይ የአንድ የፖለቲካ ድርጅት ጥያቄ ሳይሆን አስፈላጊ እና የትውልድ ጉዳይ መሆኑን በመረዳት ሁሉም ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲው የምጣኔ ኃብት መምህር የሆኑት አቶ ሁሳ አሎ በበኩላቸው፥ኢትዮጵያ የባህር በር በማጣቷ ምክንያት ለከፍተኛ የወደብ ኪራይና ሌሎች ኢኮኖሚያዊና ጂኦ ፖለቲካዊ ጫናዎች ስር መውደቋ የሚያስቆጭ መሆኑን አስታውሰዋል።
በዚህም ለተለያዩ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ይውል የነበረው ከፍተኛ ገንዘብ ለወደብ ኪራይ እንደሚውል ጠቅሰው፥ መንግስት የባህር በር ጉዳይ የህልውና ጉዳይ አድርጎ መያዙ ተገቢ አጀንዳ ነው ሲሉም አውስተዋል።