በክህሎት ኢትዮጵያ መርሃ ግብር በቴክኖሎጂ ማበልጸጊያ በተከናወኑ ስራዎች አስደናቂ ውጤቶች እየተገኙ ነው - ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል - ኢዜአ አማርኛ
በክህሎት ኢትዮጵያ መርሃ ግብር በቴክኖሎጂ ማበልጸጊያ በተከናወኑ ስራዎች አስደናቂ ውጤቶች እየተገኙ ነው - ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 19/2018(ኢዜአ)፦ በክህሎት ኢትዮጵያ መርሃ ግብር በቴክኖሎጂ ማበልጸጊያ ከወጣቶች ጋር በተከናወኑ ስራዎች አስደናቂ ውጤቶች እየተገኙ መሆኑን የስራና ከህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።
በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የተመረቱ የተኪ ምርት ቴክኖሎጂዎች ማስተዋወቂያ ፕሮግራም እየተካሄደ ይገኛል።
ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ችግሮችን ወደ ዕድል ለመቀየር ከሚተጉ ወጣቶች ጋር የሚከናወኑ ተግባራትን በማጠናከር ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እየተሰራ ነው።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በተካሔደው በክህሎት ኢትዮጵያ ፕሮግራም የቴክኖሎጂ ማበልጸጊያ ስራዎች ከወጣቶች ጋር በተከናወኑ ስራዎች አስደናቂ ውጤቶች እየተገኙ ነው ብለዋል።
ችግር ፈቺና በርካታ ስራዎችን ማከናወን የሚያስችሉ አማራጮች ያሏቸው ቴክኖሎጂዎች በስፋት እየተመረቱ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም የፈጠራ ሰራዎችን ወደ ምርት ለማስገባት የግሉ ዘርፍ በስፋት እንዲሰማራም ጠይቀዋል።
በዛሬው እለት በተካሔደው መርሃ ግብር ላይ የቀረቡት ቴክኖሎጂዎች በመደመር እሳቤ ክህሎትና እውቀትን በጋራ መምራት እንደሚቻል የሚያመላክቱ ናቸው ብለዋል።
የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ፈጠራን ማበረታታት ፍጥነትን ማሳደግ የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ ነን ሲሉም ገልጸዋል።
በኢንስቲትዩቱ ለመጀመሪያ ጊዜ አዳዲስ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎች መመረታቸውንም ተናግረዋል።
ለአብነትም ለመጀመሪያ ጊዜ የኢንዳክሸን ሞተር መሰራቱን ፣ የኤሌትሪክ ተሸከርካሪዎች ቻርጅ ማድረጊያ ቴክኖሎጂ ፣ ስማርት የመንገድ ዳር መብራቶች መሰራታቸውን ጠቅሰዋል።
በቴክኖሎጂ ማስተዋወቂያ መርሃ ግብሩ ላይ ስራዎቻቸውን ካቀረቡት መካከል በኢንስቲትዩቱ የቴክኖሎጂ ዲፓርትመንት ቴክኖሎጂ ዴስክ ሀላፊ አቶ ወጋየው ሙሉነህ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢንዳክሸን ሞተር መስራቱን ገልጸው፤ ፈጠራውን ማንኛውንም ሞተር ማንቀሳቀስ የሚያስችል ለኢንዱስትሪዎች ትልቅ ጠቀሜታ ያለውና የውጭ ምንዛሬ ወጪን መቀነስ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
በቴክኖሎጂ ፈጠራ የተሰማራው ወጣት አቤል ማሰረሻ በበኩሉ ስማርት የመንገድ ዳር መብራቶች መስራቱን ገልጾ ዘመናዊ ቴክኖሎጂው ከመብራት አገልግሎት በተጨማሪ ካሜራና ሌሎች ሴንሰሮች ያለው በመሆኑ መረጃ እንደሚሰበሰብም ጠቁሟል።