ቀጥታ፡

የግብርናውን ዘርፍ ተወዳዳሪነትና ዘላቂነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ ፕሮግራሞች ይፋ ሆኑ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 19/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን የግብርናውን ዘርፍ ተወዳዳሪነትና ዘላቂነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ ሁለት ፕሮግራሞች ይፋ አድርጓል።

ሁለተኛው ቀጣናዊ የእጽዋትና እንስሳት ጤና አጠባበቅ ጉባዔ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል፡፡

ጉባኤውን የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣንና የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራቾችና ላኪዎች ማህበር በጋራ አዘጋጅተውታል።


 

በመርኃ ግብሩ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለሰ መኮንን(ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ድሪባ ኩማን ጨምሮ አጋር አካላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን የግብርና ምርቶችን ወደ ውጭ የመላክ ሂደትን የሚያቀላጥፉና የጥራት ደረጃን የሚያሻሽሉ ኢ-ፋይቶ(ePhyto) እና ማኅበር(MAHEBER) የተሰኙ ፕሮግራሞችን በይፋ አስጀምሯል።

ኢ-ፋይቶ የእጽዋት ጤና የምስክር ወረቀት በኤሌክትሮኒክ የሚሰጥበት ስርዓት ሲሆን አገልግሎቱ የግብርና ምርቶችን ወደ ውጭ የመላክ ሂደትን ፈጣንና ደህንነቱ የተጠበቀ ያደርገዋል ተብሏል።

ማኅበር ደግሞ የኢትዮጵያን ሆርቲካልቸር ዘርፍ ተወዳዳሪነት፣ የጥራት ደረጃንና ዘላቂነትን ለማሳደግ ያለመ ፕሮግራም መሆኑ ተጠቁሟል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለሰ መኮንን(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ የSPS(Sanitary and Phytosanitary Measures) ወይም የእንሰሳት እና እጽዋት ጤና አጠባበቅ ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን ማሟላት ለወጭ ንግድ መሳለጥ ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል።

የእንሰሳት እና እጽዋት ጤና አጠባበቅ(SPS) የዓለም አቀፍ ንግድ ደህንነትንና ጥራትን የሚያረጋግጥ ስርዓት መሆኑን ጠቁመው፤ ለዓለም አቀፍ ንግድና ለባዮሴኩሪቲ መሠረት መሆኑን ገልጸዋል።

የፕሮግራሞቹ መጀመር የግብርናውን ዘርፍ ተወዳዳሪነትና ዘላቂነት ለማረጋገጥ ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢ-ፋይቶ ስርዓት በወረቀት ላይ የተመሠረተውን አሰራር በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመተካት ለኤክስፖርት ንግድ ቅልጥፍና፣ ግልጽነት እና አስተማማኝነት በእጅጉ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

ፕሮግራሞቹ በተለይም የሆርቲካልቸር ዘርፉን ለማጠናከር፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ለአርሶ አደሮችና አምራቾች የተሻለ የገበያ ተደራሽነትን መፍጠር የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የግብርና ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ድሪባ ኩማ በበኩላቸው፤ ኢ-ፋይቶ ስርዓት የምስክር ወረቀት አሰጣጥን ቀላል፣ ፈጣንና ወጪ ቆጣቢ እንደሚያደርገው ጠቅሰዋል።

ባለስልጣኑ 66 አገልግሎቶችን በኦንላይን ለመስጠት የሚያስችሉ ከ4 ሺህ በላይ መረጃዎችን በመሰነድ የዲጂታል አገልግሎት መጀመሩን ገልጸዋል።

ከአገልግሎቶቹ መካከል 29 የሚሆኑት በመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ተካተው እየተሰጡ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም