የሉሲ እና ሰላም ቅሪተ አካል በቼክ ሪፐብሊክ በነበራቸው ቆይታ የኢትዮጵያን ምድረ ቀደምትነት አሳይተዋል - ኢዜአ አማርኛ
የሉሲ እና ሰላም ቅሪተ አካል በቼክ ሪፐብሊክ በነበራቸው ቆይታ የኢትዮጵያን ምድረ ቀደምትነት አሳይተዋል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 19/2018(ኢዜአ)፦የሉሲ(ድንቅነሽ) እና ሰላም ቅሪተ አካል በቼክ ሪፐብሊክ በነበራቸው ቆይታ የኢትዮጵያን ምድረ ቀደምትነት በድጋሜ ማሳየት መቻላቸውን የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ ገለጹ።
የሉሲ(ድንቅነሽ) እና ሰላም ቅሪተ አካል በቼክ ሪፐብሊክ ፕራግ ብሔራዊ ሙዝየም ለህዝብ እይታ ቀርበው ቆይተዋል።
የሉሲ(ድንቅነሽ) እና ሰላም ቅሪተ አካል በመካከለኛው አውሮፓ ቼክ ሪፐብሊክ የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀው ወደ ብሔራዊ ሙዝየም ተመልሰዋል።
በኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን በተደረገው አቀባበል የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ፣ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው (ረ/ፕ)፣ በኢትዮጵያ የቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደር ሚሮስላቭ ኮሴክ እና የፕራግ ብሔራዊ ሙዝየም ዳይሬክተር ጀነራል ሚካኤል ሉኬሽ ተገኝተዋል፡፡
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ባለብዙ መልኳ ኢትዮጵያ የበርካታ የቱሪዝም ሀብቶች ባለቤት ናት።
ኢትዮጵያ የሉሲና ሰላም ቅሪተ አካልን ጨምሮ የሰው ዘርን አመጣጥ የሚያስረዱ ጥንታዊ ቅርሶች ያሏት ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።
ቅሪተ አካላቱ የሰው ልጅ ስለራሱ የሚማርባቸው ዓለም የሚዘክራቸው እና ኢትዮጵያም የምትኮራባቸው የከበሩ ሀብቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ እና በቼክ ሪፐብሊክ መካከል በተደረገ ስምምነት ቅርሶቹ በቼክ ሪፐብሊክ ፕራግ ሙዝየም ለ60 ቀናት መቆየታቸውን ገልጸዋል።
የሉሲ(ድንቅነሽ) እና ሰላም ቅሪተ አካል በቼክ ሪፐብሊክ በነበራቸው ቆይታ የኢትዮጵያን ምድረ ቀደምትነት አሳይተዋል ብለዋል፡፡
የትላንቷን ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በእድገት ግስጋሴ ላይ ያለችውን የዛሬይቱን እና በተስፋ የፈካችውን የነገዋን ኢትዮጵያ ለመላው ዓለም ማስተዋወቃቸውን ተናግረዋል።
ቅርሶቹ ከወጡበት ጊዜ አንስቶ እስኪመለሱ ድረስ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረጉን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደር ሚሮስላቭ ኮሴክ በበኩላቸው ቅሪተ አካላቱ በሰላም መመለሳቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ዕድሉን ስለሰጠን እናመሰግናለን ያሉት አምባሳደሩ፤ ቅሪተ አካላቱ በበርካታ ሰዎች በመጎብኘታቸው ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል፡፡