ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ በእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ላይ የሚከናወኑ ተግባራትን ለማጠናከር ትኩረት ተሰጥቷል - ሚኒስትር አዲሱ አረጋ    

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 19/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ በእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ላይ የሚከናወኑ ተግባራትን ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ  የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ ገለጹ።

በተቀናጀ የእንስሳት ልማት፣ የስጋ ወጪ ንግድ የእርድ እንስሳት አቅርቦት ትስስር ላይ ያተኮረ የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ ተካሂዷል፡፡       


 

የግብርና ሚኒስትር አቶ አዲሱ አረጋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በዓለም ደረጃ ተጠቃሽ ቁጥር ያለው የእንስሳት ሀብት ቢኖራትም ተገቢውን  ጥቅም እያገኘች አይደለም፡፡ 

ወደ ውጭ የሚላከውም ካለን አቅም አኳያ ዝቅተኛ ነው ያሉት ሚኒስትሩ በመስኩ ያሉ ችግሮችን በመፍታት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል፡፡  

የእንስሳት እርባታውን ዘመናዊ ማድረግ ሌላው የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ገልጸው፤ ዘመናዊ እንስሳት እርባታ ማዕከላትን ወደ ስራ ማስገባት ሥራው እንደሚጠናከር አመልክተዋል።  

በእንስሳት ዝርያ ማሻሻል በኩል የዳልጋ ከብቶችና ዶሮዎች ላይ የተሻለ አፈጻጸም መኖሩን ገልጸው፤ በግና ፍየሎች ዝርያ ማሻሻል ላይ ግን በሚጠበቀው ደረጃ አልተጓዝንም፤ የበለጠ መሥራት ይጠበቅብናል  ሲሉም  ተናግረዋል።  

በእንስሳት አቅርቦት ላይ ሕገ ወጥ ደላላ እና ተደራራቢ ቀረጥ መኖሩ ለዘርፉ ትልቅ ማነቆ መሆኑን አመልክተው ማነቆው በዘላቂነት እንዲፈታ ባለድርሻ አካላት በተቀናጀ አግባብ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።  


 

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ በበኩላቸው፤በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመለየት መፍትሄዎችን ያመላከተ የ5 ዓመት ስትራቴጂ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።          

ስትራቴጂው ዘመናዊ የእንስሳት እርባታ ሥርዓትን መዘርጋት፣ማኀበረሰብን መሰረት ያደረገ እርባታዎችን ድጋፍና ክትትል ማድረግ የሚያስችሉ ግቦች የተካተቱበት መሆኑን አብራርተዋል። 

የእንስሳት ምርት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ የእንስሳት ጤና ማስጠበቅ ወሳኝ ነው ያሉት ሚኒስትር ደኤታው፤ ክትባት፣የእንስሳት ክሊኒክ ተደራሽነት ማስፋት እንዲሁም የእንስሳት ጤና ባለሙያዎች ማፍራት በስትራቴጂው መሰረት የሚተገበር መሆኑን አስረድተዋል።    

የኤክስፖርት ቄራዎችን የማምረት አቅም ማሳደግ፣ለቄራዎች የሚቀርበውን እንስሳት አቅርቦት ችግር መፍታት የተቀመጡ ሌሎች የመፍትሄ አቅጣጫዎች መሆኑንም አብራርተዋል።


 

የመስኖና ቆላማ አከባቢ ሚኒስትር ዴኤታ እንድሪያስ ጌታ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤በቆላማ አካባቢዎች የእንስሳት መኖ አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ዝናብና መስኖን በመጠቀም መኖ እየተመረተ ነው። 

የእንስሳት ጤና ክሊኒኮች የማስፋፋት ሥራው በትኩረት እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል።  

የኢትዮጵያ እንስሳት ልማት ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አስራት ጤራ በበኩላቸው፤ በእንስሳት አቅርቦት ላይ የኀብረት ሥራ ማህበራትን በስፋት ማሳተፍ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ለዚህ ደግሞ ያሉባቸውን የፋይናንስ አቅርቦት ችግር መፍታት ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም