ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ብሔራዊ ጥቅምን የማረጋገጥና ታሪካዊ ስብራትን የመጠገን አጀንዳ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 19/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ብሔራዊ ጥቅምን የማረጋገጥና ታሪካዊ ስብራትን የመጠገን አጀንዳ መሆኑን ምሁራን ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ የቀይ ባህር ጉዳይ ሕጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልክዓ ምድራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሠመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት መሀመድ ዑስማን (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ ቀይ ባሕር የዓለም አቀፍ ጂኦ ፖለቲካል የስበት ማዕከል የምስራቅ አፍሪካ የሰላምና ደኅንነት አንኳር መስመር ነው፡፡


 

ቀይ ባህር የብሔራዊ ደህንነትና ሉዓላዊነት ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ቀይ ባህርን ያጣችበትን ኢ-ርቱዕ እና ኢ-ፍትሐዊ ታሪካዊ ስህተትን ለማረም የተጀመረው ጥረት ተገቢና ሀገራዊ አጀንዳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የነፃነት ቀንዲል፣ የዓለም አቀፍና አህጉራዊ ተቋማት መስራችና መገኛ ሰፊ ህዝብና በፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ ያለች ሀገር መሆኗን ገልጸው፤ የዚህ ዘመን ትውልድ ኢትዮጵያ የባህር በር ያስፈልጋታል ብሎ መነሳቱ ወሳኝ ምዕራፍ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በራሷ የባህር በር ባይተዋር መሆን የለባትም ያሉት መሀመድ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ብሔራዊ ጥቅምን የማረጋገጥና ታሪካዊ ስብራትን የመጠገን አጀንዳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያን የሚያክል የግዙፍ ታሪክ፣ ብዙ ህዝብ ባለቤትና የአፍሪካ ጉዳዮች ፊት አውራሪ ሀገር የባሕር በር ባለቤትነት ስብራቷ ሳይጠገን ለትውልድ መተላለፍ የለበትም ብለዋል፡፡

የዓለም አቀፍ የሕግ ተመራማሪና መምህር ደጀኔ የማነ በበኩላቸው፤ ዓለም አቀፍ ሕጎችና የመንግስታቱ ድርጅት የባሕር ስምምነቶች የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምክንያታዊነት ያጎላዋል ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ የባሕር በር ባለቤትነት ለዘመናት ራሱን ችሎ የቆመ መሆኑን በማንሳት፤ ከሌላ ሀገር የግዛት አንድነት ጋር ተደርቦ የሚታይ አይደለም ብለዋል፡፡

ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በኋላ በአልጀርስ ስምምነት የሀገራቱ የድንበር ውዝግቦች ተቀባይነት በሌላቸው የቅኝ ግዛት ውሎች እንዲዳኙ ይሁንታ መሰጠቱም አሳዛኝ ክስተት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአልጀርስ ስምምነትና በፊት የነበሩ የቅኝ ግዛት ውሎችን መነሻ በማድረግ የተፈጸመባትን መሠረታዊ የውሳኔ መዛነፍ እንደገና እንዲከለስ የማድረግ መብቷን መጠቀም ትችላለች ብለዋል፡፡

ለዚህም የተጠና እና የተደራጀ የዓለም አቀፍ የሕግ ጥናት በማካሄድና ዓለም አቀፍ ልማዳዊ ሕግጋትን ጭምር በማካተት የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የፖሊሲና ስትራቴጂ ተመራማሪ ተመስገን ዋለልኝ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ ለሶስት አስርት ዓመታት ከባሕር በር ተገልላ የጂኦ-ፖለቲካ እስረኛ ሆና መቆየቷን ገልጸዋል፡፡


 

ኢትዮጵያ ከባሕር በር እንድትገለል የተፈጸመባት ደባ እንደሚያስቆጭ ገልጸው፤ በዓለም አቀፍ የወጪና ገቢ የንግድ ሥርዓት ተወዳዳሪነቷ ላይ ጫና አሳድሮባታል ብለዋል፡፡

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ እና መሰል ሀገራዊ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዳይጠናቀቁ አሉታዊ ጫና ማሳደሩን አስታውሰው፤ የኢትዮጵያን ግዙፍ ኢኮኖሚና የሎጂስቲክስ ዕድገት የሚሸከም በባለቤትነት የሚተዳደር ከአንድ በላይ የወደብ አገልግሎት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም