አዳማ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ ለመሆን ዝግጅት እያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አዳማ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ ለመሆን ዝግጅት እያደረገ ነው
አዳማ ፤ ጥቅምት 19/2018 (ኢዜአ)፡- አዳማ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ ለመሆን የቅድመ ዝግጅት ተግባር እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ለሚ ጉታ(ዶ/ር) ፤ ተቋሙ የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ለሀገር እድገት በሚገባው ልክ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ራስ ገዝ ለመሆን እየተዘጋጀ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ተከትሎ ራስ ገዝ ለመሆን የትምህርት ሚኒስቴር መስፈርቶችን ማሟላት በሚያስችል አግባብ ላይ እንደሆነ ተናግረዋል።
ከዝግጅቱም ውስጥ የተቋማዊ ግምገማ ሠነድ፣ ስትራቴጂክ እቅድ፣ፖሊሲና መመሪያዎች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
ይህንንም ተከትሎ ዩኒቨርስቲው ራስ ገዝ (የአውቶኖመስ) የመሆን ጥያቄውን ለትምህርት ሚኒስቴር በይፋ ማቅረቡን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አስታውቀዋል።
በተለይ የመማር ማስተማር፣የምርምር እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግ የመሰረተ ልማት ግንባታ ላይም ዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ከነዚህ ስራዎች ውስጥ ባለፈው በጀት ዓመት የተጠናቀቀው የምርምር ፓርክ ግንባታን አንስተዋል።
በዚህ የምርምር ፓርክ ውስጥ ለሚገኙ አምስት የልህቀት ማዕከላት 30 ቤተ ሙከራዎችን የማደራጀት ስራ ተጀምሯል ብለዋል።
ይህ ፓርክ ከዩኒቨርሲቲው ባሻገር እንደ ሀገር በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ግዙፍ እና ልዩ የምርምር ማዕከል በመሆን የላቀ ፋይዳ እንደሚኖረው አስረድተዋል።
በተጨማሪም በዩኒቨርሲቲው ዘመናዊ የዳታ ማዕከል፣የ10 ኪሎ ሜትር አስፋልት እና አራት ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ መንገድና ሌሎችም ግንባታዎች እየተገባደዱ ይገኛሉ ብለዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1294/2015 በአብላጫ ደምፅ ማጽደቁ ይታወሳል።
አዋጁ ለሀገር ዕድገት ትልቅ አስተዋፅኦ የሚያደርጉ በቴክኖሎጂ፣ በፈጠራና በምርምር የላቀ እውቀት ያለው የሰው ኃይል ለማፍራት የሚሰሩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ለመገንባት ያለመ ነው።
ከዚህም ባለፈ ዩኒቨርሲቲዎቹ ሙያዊ ተልዕኳቸውን በላቀ ብቃት ተመራማሪዎችን ለማፍራት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው ።
የጥናትና ምርምር፣ የትምህርትና የማህበረሰባዊ ነጻ አገልግሎት የሚያከናውኑበትን የፋይናንስ ምንጭ መሰብሰብና ሀገራዊ ልማትን ማገዝ የሚችሉበትን ነጻ ምህዳር ለመፍጠር ትልቅ ዕገዛ እንዲኖረው ተደርጎ በውይይት ዳብሮ መዘጋጀቱን በወቅቱ ተጠቅሷል።