ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ሰላም አስፈላጊውን ድጋፍ ታደርጋለች- የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ሰላም አስፈላጊውን ድጋፍ ታደርጋለች- የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 19/2018 (ኢዜአ):- ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ሰላም እና መረጋጋት የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።
ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ጋር በመሰረተ ልማት ያላትን ትስስር ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላትም ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በደቡብ ሱዳን የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስቴር ፒዬንግ ዴንግ ኩኦል የተመራ ከፍተኛ ልዑክ ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ልዑካን ቡድኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በደቡብ ሱዳን በተለይም በአቢዬ ግዛት ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ገለጻ አድርጓል።
ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን አጠናቃ በስኬት በማስመረቋ ደስታቸውን በመግለጽ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት በህዳሴ ግድብ ምርቃት ላይ በመሳተፋቸውም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ሰላም እና መረጋጋት ያላትን ጽኑ ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
ሁለቱ ሀገራት በመሰረተ ልማት የበለጠ በመተሳሰር ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትብብርን ለማጎልበት ሊሰሩ እንደሚገባም መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።