ቀጥታ፡

በምዕራብ ወለጋ ዞን የተሻሻሉ የፍራፍሬ ዝርያዎችን የተጠቀሙ አርሶ አደሮች ውጤታማ ሆነዋል

ጊምቢ፤ ጥቅምት 19/2018 (ኢዜአ)፡-በምዕራብ ወለጋ ዞን ከግብርና ማዕከል የወጡ የተሻሻሉ የፍራፍሬ ዝርያዎችን የተጠቀሙ አርሶ አደሮች ከልማቱ የተሻለ ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ በፍራፍሬ ልማት ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮች ከመንግስት ባገኙት የተሻሻሉ የፍራፍሬ ዝርያዎችን ተጠቅመው በማልማት ገቢ አግኝተው የተሻለ ኑሮ መምራት መጀመራቸውን ገልጸዋል።


 

የተሻሻሉ ዝርያዎቹን ከተጠቀሙ አርሶ አደሮች መካከል በዞኑ የሆማ ወረዳ ነዋሪው አቶ ተካልኝ ኤፍሬም፣ ከዚህ በፊት በቡና ልማት ላይ ብቻ ጥገኛ ሆነው መቆየታቸውን ተናግረዋል።


 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ ዝርያቸው የተሻሻሉ ፍራፍሬዎችን በመጠቀም በማልማታቸው ውጤታማ መሆን መቻላቸውን ገልጸዋል።

አቮካዶና ሙዝ በማልማት በዓመት እስከ 25 ሺህ ብር ገቢ እያገኙ መሆኑን አንስተው በዚህም ህይወታቸውን በተሻለ መንገድ እየመሩ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የላሎ አሳቢ ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር ገረመው ጅሬኛ በበኩላቸው ከግብርና ማዕከል የወጣ የተሻሻለ የሙዝ ዝርያን በማልማት ኢኮኖሚያቸው እያደገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡


 

በቀጣይ ልማቱን በማጠናከር የሙዝ ዝርያዎችን በማባዛትና በማልማት ተጠቃሚነታቸውን የበለጠ ለማሳደግ ተግተው እንደሚሰሩም ጠቅሰዋል፡፡

በምዕራብ ወለጋ ዞን የግብርና ጽህፈት ቤት የፍራፍሬ ልማት ባለሙያ አቶ ጂብሪል መንጌ እንደገለጹት በዞኑ በሁሉም ወረዳዎች የፍራፍሬ ልማት በሰፊው እየተካሄደ ነው።

በእስካሁኑ እንቅስቃሴ በ40 ሺህ 381 ሄክታር መሬት ዝርያቸው የተሻሻሉ ፍራፍሬዎች በኩታ ገጠም እየለሙ መሆኑን ገልጸው በልማቱም ከ62 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች መሳተፋቸውን ተናግረዋል።


 

ባለፉት ዓመታት ከግብርና ማዕከላት የወጡ ዝርያቸው የተሻሻሉና በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዛትና ጥራት ያለው ምርት የሚሰጡ ሙዝ፣ አቮካዶ፣ ፓፓያና ሌሎች ፍራፍሬዎች ለአርሶ አደሮቹ ተደራሽ መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

እየተከናወነ ከሚገኘው የፍራፍሬ ልማት ከሁለት ሚሊዮን 291 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት በየዓመቱ እየተሰበሰበ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡

አርሶ አደሩ በአንድ ዙር ምርት በአማካኝ ከ30 ሺህ እስከ 50 ሺህ ብር ገቢ እያገኘ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለአብነትም በተያዘው የምርት ዘመን ፍሬ መስጠት ከጀመረ ‘ሓሽ’ ከተባለ የአቮካዶ ዝርያ 76 ኩንታል ምርት ለገበያ ማቅረብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም