ቀጥታ፡

የማዳበሪያ ፋብሪካው መገንባት  ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ያስችላል 

ጎንደር፤  ጥቅምት 19/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ በቅርቡ ይፋ ያደረገችው የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ምርትና ምርታማነትን ይበልጥ በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥና የዘርፉን የውጪ ምንዛሬ የማመንጨት አቅምን ማጎልበት እንደሚያስችል ተመላከተ። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተመረቀበት ወቅት ጉባ ላይ ይፋ ካደረጓቸው ግዙፍ የግንባታ ፕሮጀክቶች መካከል የማዳበሪያ ፋብሪካው ተጠቃሽ ነው። 

ኢዜአ ያነጋገራቸው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ዲንና ምሁር ካህሌ ጀንበር (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ መንግስት ሜጋ ፕሮጀክቶችን በመተግበር የወሰደው ኢንሼቲቭ የኢትዮጵያን እድገት ለማፋጠን የሚያስችል ነው። 

በተለይ የማዳበሪያ ፋብሪካው መገንባት የድህነት ታሪክን በመሰረዝ አዲስ የታሪክ ምዕራፍን ለማብሰር ፋይዳው የጎላ መሆኑን አመልክተዋል። 


 

የፋብሪካው ግንባታ ሲጠናቀቅም ማዳበሪያን በብዛትና በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ያስችላል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለማዳበሪያ ግዢ በየዓመቱ የምታወጣውን ከፍተኛ ገንዘብ በማስቀረት ለሌሎች የልማት ስራዎች ለማዋል እንደሚያግዝም ተናግረዋል።

በተጨማሪም ሀገሪቱ ወደ ውጪ የምትልከውን የግብርና ምርት በማሳደግ የዘርፉን የውጪ ምንዛሬ የማመንጨት አቅምን በማጎልበት በኩል ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ከፍ ያለ መሆኑን አስረድተዋል።

በምግብ ራስን መቻል የኢትዮጵያ የሉዓላዊነትና የህልውና ጉዳይ ነው ብለዋል።  

ምሁራን አርሶ አደሩ በሳይንሳዊ የማዳበሪያ አጠቃቀም ላይ ያለውን የእውቀትና የክህሎት ክፍተት በጥናትና ምርምር በመታገዝ የመለወጥ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲም የምርምር ምክረ ሃሳቦችን በማፍለቅና የኤክስቴንሽን ስርጸትን በማጎልበት አርሶ አደሩ ሳይንሳዊ የማዳበሪያ አጠቃቀምን በማሻሻል የሚጠበቀውን ምርት እንዲያመርት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታንና የመጀመሪያውን የጋዝ ማውጣት ስራ በማጠናቀቅ የማዳበሪያ ፋብሪካና የነዳጅ ማጣሪያ ለመገንባት የወሰደችው ቁርጠኛ አቋም የግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት እንደሚያደርጋትም ምሁሩ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም