ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የሚገባትን የባሕር በር መጠየቋ ቅንጦት አይደለም - ምሁራን

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 19/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ መልማቷን ባልፈለጉ አካላትና ማስረጃ በሌለበት ሁኔታ በዐሻጥር የተቀማችውን የባሕር በር መጠየቅ መብቷ እንጂ ቅንጦት እንዳልሆነ ምሁራን ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በትላንትናው እለት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ተካሂዷል።

በዚሁ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቀይ ባሕር ጋር በተያያዘ በሰጡት ማብራሪያ፤ የቀይ ባሕር ጉዳይ ሕጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልከዓ-ምድራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ መሆኑን ኢትዮጵያ ታምናለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ ቀይ ባሕርን እንድታጣ የወሰነው ማን ነው ብለን ስንፈትሽ ማስረጃ አልተገኘም፤ ተቋማትም እንዳልገቡበት አንስተዋል።

ባሕር በር የኅልውና ጉዳይ በመሆኑ ኢትዮጵያም ተዘግቶባት መኖር ስለማትችል ጥረቷ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን በጉዳዩ ላይ እንዳሉት ኢትዮጵያ ብልጽግናዋን ባልፈለጉ አካላት በተንኮል የተነጠቀችውን የአካሏን ክፋይ መጠየቅ መብቷ እንጂ ቅንጦት እንዳልሆነ አስረድተዋል።

የዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር እንዳለ ንጉሴ፤ ኢትዮጵያ የባሕር በሯን ያጣችበት ሂደት ግፍ እንጂ ሕጋዊ አለመሆኑን አንስተው፤ መንግሥት ኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት እንዳለባት አምኖ አጀንዳ ማድረጉ ከሕግም ሆነ ከሞራል አንጻር ትክክል መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በዐሻጥር የተቀማችውን የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገውን ዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንድታጠናክርም መክረዋል።

በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና ተመራማሪ ያሬድ አያሌው (ዶ/ር) በበኩላቸው የኢትዮጵያ የባሕር በር ተጠቃሚ መሆን ፋይዳው የቀጣናውም ጭምር እንደሚሆን አስረድተዋል።

ቀጣናውን ጨምሮ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያ የጠየቀችው የአካሏን ክፋይና ህጋዊ መብት መሆኑን በመገንዘብ ለጋራ ተጠቃሚነት ሲሉ ኢትዮጵያ የባሕር በር እንድታገኝ ማገዝ እንደሚጠበቅባቸው አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም