ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሐብትንና አካባቢን ለመጠበቅ እያከናወነችው ያለው ተግባር በዓለም አቀፍ ደረጃ በአርዓያነት የሚወሰድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሐብትንና አካባቢን ለመጠበቅ እያከናወነችው ያለው ተግባር በዓለም አቀፍ ደረጃ በአርዓያነት የሚወሰድ ነው
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 19/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሐብትንና አካባቢን ለመጠበቅ እያከናወነችው ያለው ተግባር በዓለም አቀፍ ደረጃ በአርዓያነት ሊወሰድ የሚችል ነው ሲሉ በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደርና የአፍሪካ ህብረት ቋሚ ተወካይ አኒል ኩማር ገለጹ፡፡
ኢትዮጵያ በብዝሃ የአየር ንብረት የታደለች፤ ልዩ ልዩ የተፈጥሮ ሀብቶችን የያዘች፣ በርካታ እፅዋቶችና የዱር እንስሳት ዝርያዎች የሚገኙባት መሆኗን አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡
አምባሳደሩ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሐብትንና አካባቢን ለመጠበቅ እያከናወነችው ያለው ተግባር በዓለም አቀፍ ደረጃ በአርዓያነት ሊወሰድ የሚችል ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለው የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ የአገሪቱን የደን ሽፋን ከማሳደግ ባለፈ ለብዝሃ ህይወት መጎልበት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው ስራው አስደናቂ መሆኑን ተናግረዋል።
በአፋር ክልል የሚገኘው ዝቅተኛው የደናክል በረሃ እና የተለየ የአየር ንብረት ያለው የስምጥ ሸለቆ መነሻ ኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ አረንጓዴ የሆኑና ከፍተኛ የዝናብ መጠን የሚያገኙ ደጋማ አካባቢዎችን የያዘች መሆኗንም ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ ያሉ ልዩ ልዩ የአየር ንብረት ጸባዮች፣ የዕጽዋትና የዱር እንስሳት ዝርያዎች ሀገሪቱን ብዝሃ ተፈጥሮ የተቸራት አድርጓታል ብለዋል፡፡
ይህም የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን በማስፋት ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አመላክተዋል፡፡
አምባሳደሩ በኢትዮጵያ የተተገበሩ እንደ አረንጓዴ አሻራ ያሉ መርሃ-ግብሮችና ሰፋፊ የልማት ስራዎች ለሀገሪቱ የወደፊት ብልፅግና ከፍተኛ ፋይዳ እንዳላቸው ጠቅሰው ፤ የተተከሉት ዛፎች እንዲጸድቁ የሚደረገውን እንክብካቤ አድንቀዋል።
በቀጣዩች አስር ዓመታት ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አስደማሚ ለውጦችን ታስመዘግባለች ሲሉም ገልጸዋል።
ህንድ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብት ላይ ለምታከናውነው ተግባር አድናቆት እንዳላት ጠቁመው፤ አገራቸው በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ አስፈላጊነት ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይ አቋም እንዳላት ተናግረዋል፡፡
ህንድ እና ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ የጋራ ስምምነት እንዳላቸው አስታውሰው፡ ትብብሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር እና በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ያከናወነቻቸው ተግባራት የአዕዋፋትንና የዱር እንስሳትን ስደት ትርጉም ባለው መልኩ መቀነሱ ይታወቃል፡፡