ቀጥታ፡

በመዲናዋ የተማሪዎችን ውጤት ለማላቅ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ትውልድን ለማነፅ አቅም ፈጥረዋል

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 19/2018(ኢዜአ)፦በመዲናዋ የተማሪዎችን ውጤት ለማላቅ የተከናወኑ ተግባራት የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ውጤታማ ትውልድን ለማነፅ አቅም መፍጠራቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ትናንት ለምክር ቤቱ አባላት በሀገሪቱ የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

መንግስት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በትምህርት ለትውልድ እንቅስቃሴ የትምህርት ተቋማትን ምቹ የማድረግና የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች ተደራሽ በማድረግ እንዲሁም የተማሪዎች የምገባ መርሀ ግብር ማከናወኑ እየሰራቸው ካሉ ተግባራቶች ውስጥ ተጠቃሽ መሆናቸውን አንስተዋል።

በዘንድሮው የትምህርት ዘመንም ከ43 ሚሊየን በላይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የመማሪያ መጻሕፍት መታደሉንና ይህም የትምህርት ጥራትን ለማምጣት ከተሰሩ ስራዎች መካከል ተጠቃሽ መሆኑን ገልፀዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) በመዲናዋ ትውልድን የሚያንጹ ተግባራት  ተጠናክረው መቀጠላቸውን አስታውቀዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ህብረተሰቡን በማሳተፍ ትምህርት ቤቶችን በመሰረተ ልማት ምቹ የማድረግ፣ የግብዓት አቅርቦትና የተማሪዎች ምገባን የማጠናከር ስራ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም በትምህርት ለትውልድ እንቅስቃሴ ከተለያዩ አካላት ሀብት በማሰባሰብ የትምህርት ተቋማትን መሰረታዊ ችግሮች መፍታት መቻሉን ተናግረዋል።

የምገባና የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችን በወቅቱ ማቅረብ በመቻሉ ተማሪዎች ትምህርታቸው ላይ ትኩረት እንዲያደርጉና የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ማስቻሉንም ገልጸዋል።

ትምህርት ቢሮው በከተማዋ ያሉ የ11ኛ እና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ለ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና አስቀድመው ሰፋ ያለ ዝግጅት እንዲኖራቸው ለማድረግ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ማላቂያ ስትራቴጂ በማዘጋጀት ወደ ተግባር ገብቷል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምገባ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ስንታየሁ ማሞ በበኩላቸው በተያዘው ዓመት ተማሪዎች በወቅቱ  የትምህርት ግብአት እንዲያገኙና የምገባ መርሀ ግብር በጊዜው እንዲጀመር መደረጉን ገልፀዋል። 


 

በዚህም በ253 ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ከ976 ሺህ በላይ ተማሪዎች የምገባ መርሀ ግብሩ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከ1 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች የዩኒፎርምና የደብተር አቅርቦት ተደራሽ መደረጉንም አብራርተዋል።

የለም አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት  ርእሰ መምህር ሰለሞን ዲሮ በትምህርት ለትውልድ እንቅስቃሴ ትምህርት ቤቱ ከግብአትና ከመሰረተ ልማት አኳያ የነበሩበትን ችግሮች የትምህርት ቤቱን ማህበረሰብ፣ የቀድሞ ተማሪዎች እና አጋር አካላትን በማሳተፍ መቅረፍ መቻሉን ተናግረዋል።


 

ከተሰሩ ስራዎች መካከልም የላብራቶሪ እቃዎች፣የቤተ መጽሀፍትን ሌሎች ለመማር ማስተማር ሂደት አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶች ማሟላት ተጠቃሽ መሆኑን በመግለጽ ይህም ተማሪዎች በትምህርታቸው ላይ የተሻለ እውቀት እንዲገበዩ አቅም  ፈጥሯል ብለዋል።

ትምህርት ቤቱ በዘንድሮ የትምህርት ዘመን 426 የቅድመ መጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ ይገኛል ያሉት ደግሞ  የአዲስ ራዕይ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህርት እየሩሳሌም ተሾመ ናቸው።


 

መንግሥት ለቅድመ አንደኛ ደረጃ ተማሪዎች በሰጠው ልዩ ትኩረት ህጻናት በተሟላ ግብዓት እና በአማረ ሁኔታ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ መደረጉን ገልፀዋል።

በተለይም የተማሪዎች ምገባ መርሀ ግብር ህጻናት ከትምህርት ገበታቸው እንዳይቀሩ ማስቻሉን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም