ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ቀይ ባህርን ለማጣት የወሰደባትን 30 ዓመት ወደ ቀይ ባህር ለመመለስ አያስፈልጋትም - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 19/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ቀይ ባህርን ለማጣት የወሰደባትን 30 ዓመታት ወደ ቀይ ባህር ለመመለስ ሌላ 30 ዓመታት አያስፈልጋትም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ በተካሀደበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰላምና ጸጥታን በሚመለከት በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፣ ኢትዮጵያ ቀይ ባህርን ለማጣት የወሰደባትን 30 ዓመታት ወደ ቀይ ባህር ለመመለስ ሌላ 30 ዓመታት አያስፈልጋትም ብለዋል።

የቀይ ባህር ጉዳይ ህጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልክዓ ምድራዊ(ጂኦግራፊያዊ) እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ እንደሆነ እናምናለን ሲሉም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ቀይ ባህርን ለማጣት 30 ዓመት በላይ ያህል የወሰደ ትግል እንደነበር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሀገሪቱ ወደ ቀይ ባህር ለመመለስ 30 ዓመት አያስፈልጋትም ነው ያሉት።

ይህን ጉዳይ ለመፍታት በተረጋጋ፣ በሰከነ እና በውይይት መሄድ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው፤ ለማጣት የፈጀውን ያህል ለመመለስ አይፈጅብንም ሲሉም በአጽንኦት ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የባህር በር ያጣችበት መንገድ የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ ካቢኔ ያልወሰነው፣ ተወካዮች ያላዩት መሆኑን ጠቁመው፤ ጥያቄው ይህን ትልቅ ጉዳይ ማን ወሰነው ብሎ መጠየቅ ተገቢ መሆኑን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ የባህር በር ያጣችበት መንገድ ህጋዊ እና ተቋማዊ መሠረት የሌለው እንደሆነም ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም