ቀጥታ፡

በካራባኦ ዋንጫ ዛሬ ለሩብ ፍጻሜ ለማለፍ ወሳኝ ጨዋታዎች ይደረጋሉ 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 19/2018 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ካራባኦ ካፕ አራተኛ ዙር የሁለተኛ ቀን ውሎ አምስት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።

የወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ ኒውካስትል ዩናይትድ ምሽት አምስት ላይ በሴንት ጀምስ ፓርክ ስታዲየም ቶተንሃም ሆትስፐርስን ያስተናግዳል።

ኒውካስትል ዩናይትድ አምና በካራባኦ ዋንጫ ፍጻሜ ሊቨርፑልን በማሸነፍ ዋንጫውን ለመጀመሪያ ጊዜ ማንሳቱ የሚታወስ ነው። 

ቶተንሃም ሆትስፐርስ ውድድሩን አራት ጊዜ አሸንፏል። 

ኒውካስትል በሶስተኛው ዙር ብራድፎርድ ሲቲን፣ ቶተንሃም ሆትስፐርስ ዶንካስተር ሮቨርስን አሸንፈዋል። 

በሌሎች መርሃ ግብሮች አርሰናል ከብራይተን፣ ሊቨርፑል ከክሪስታል ፓላስ፣ ስዊንሲ ሲቲ ከማንችስተር ሲቲ እና ዎልቭስ ከቼልሲ በተመሳሳይ 4 ሰዓት ከ45 ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። 

ትናንት የተጀመረው የካራባኦ ዋንጫ የአራተኛ ዙር መርሃ ግብር ዛሬ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይጠናቀቃል።  

ብሬንትፎርድ፣ ፉልሃም እና ካርዲፍ ሲቲ ለሩብ ፍጻሜ ያለፉ ክለቦች ናቸው። 

እ.አ.አ በ1960 የተጀመረው የካራባኦ ካፕ (በቀድሞ አጠራሩ የእንግሊዝ ፉትቦል ሊግ ዋንጫ) በእንግሊዝ ከአንጋፋው ኤፍ ካፕ ውጪ የሚደረገው የጥሎ ማለፍ ውድድር ነው።

ሊቨርፑል 10 ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት የውድድሩ ስኬታማ ክለብ ነው። ማንችስተር ሲቲ ስምንት እና ማንችስተር ዩናይትድ ስድስት ጊዜ ውድድሩን በማሸነፍ ይከተላሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም