በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሦስት ወራት ከ4 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሦስት ወራት ከ4 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ
ሆሳዕና፤ ጥቅምት 19/2018 (ኢዜአ):- በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በባለፉት ሦስት ወራት ከ4 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ገለፀ፡፡
የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ቀመሪያ ረሻድ ለኢዜአ እንደገለጹት ቢሮው የክልሉን የገቢ አማራጮች በማስፋትና ገቢን አሟጦ በመሰብሰብ የማህበረሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ አየሰራ ነው፡፡
የክልሉን 60 በመቶ ወጪ በውስጥ ገቢ ለመሸፈን ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው ለዚህም በክልሉ ያለውን የገቢ አማራጭ ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ በተያዘው በጀት ዓመት ከተለያዩ የገቢ አማራጮች 23 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን የጠቆሙት ወይዘሮ ቀመሪያ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ4 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል ብለዋል።
የክልሉ የውስጥ ገቢ አቅም በየጊዜው እያደገ መምጣቱን የተናገሩት ሃላፊዋ ለዚህም የገቢ አሰባሰብ አሰራር መዘመን እና የማህበረሰቡ ግንዛቤ እያደገ መምጣቱን በምክንያትነት ጠቅሰዋል፡፡
በክልሉ ከአጠቃላይ ገቢ 47 በመቶ የሚሆነው ከተጨማሪ እሴት ታክስ ግብር ከፋዮች፣ ከቫትና ከደረሰኝ የሚሰበሰብ መሆኑን ገልጸው ህብረተሰቡ ስለግብር ያለው ግንዛቤ እያደገ ቢመጣም ደረሰኝ በመቀበል ረገድ ውስንነቶች አሉ ብልዋል።፡
ይህም ክልሉ ከሚያመነጨው ገቢ የሚጠበቅበትን መሰብሰብ እንዳይችል አንድ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።፡
ይህን ችግር ለመፍታት ማህበረሰቡ ላገኘው አገልግሎት ደረሰኝ የመጠየቅ ባህሉ እንዲዳብር፣ ግብር ከፋዩም ግዴታውን በታማኝነት እንዲወጣ ቢሮው ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ በስፋት እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የገቢ ግብር ህግን ተላልፈው የሚገኙትን በተጨባጭ መረጃ በመያዝ ተጠያቂ የማድረግ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
"ግብርን በወቅቱና በታማኝነት መክፈል ልማትን ማጠናከሪያ ነው" ያሉት የሆሳዕና ከተማ ነዋሪ አቶ ደምሴ አዱኛ በበኩላቸው፣ በየዓመቱ የቤት ግብራቸውን በወቅቱና በታማኝነት እንደሚከፍሉ ተናግረዋል፡፡
ግብርን በወቅቱና በታማኝነት አለመክፈል እድገትን ወደኋላ እንደሚጎትት ጠቅሰው፣ በዘርፉ ይስተዋል የነበረው ህገወጥ አሰራር ለመከላከል የግብር አሰባሰብ ሥራውን ለማዘመን የተሰራው ሥራ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።
በከተማው በልብስ ስፌት ሥራ ላይ የተሰማራችው ወይዘሪት ሰላማዊት ዮሴፍ በበኩሏ ግብርን በወቅቱና በታማኝነት መክፈል ልማትን ለማፋጠንና ህዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ ያግዛል ብላለች።
ከከተማው የልማት ሥራዎች ተጠቃሚ በመሆኔ የሚጠበቅብኝን ግብር በወቅቱ በመክፈል ግዴታዬን እወጣለሁ ያለችው ወይዘሪት ሰላማዊት፣ ግብርን በወቅቱና በአግባቡ የመክፈል ባህል መጠናክር እንዳለበት ተናግረዋል።