ኢትዮጵያ እና ቻይና በፍትህ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ቻይና በፍትህ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 18/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ቻይና በፍትህ ዘርፍ ያላቸውን የሁለትዮሽ ትብብር የበለጠ ለማጎልበት እንደሚሰሩ አስታወቁ።
የቻይና-አፍሪካ የዐቃብያነ ሕግ የትብብር ፎረም በቻይና ጓንዶንግ ግዛት ጓንጁ ከተማ ጥቅምት 19 እና 20 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።
በፍትሕ ሚኒስትር ሀና አርዓያሥላሴ የሚመራ ልዑክ በስብስባው ላይ ይሳተፋል።
የፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ዳባ በልዑካን ቡድኑ ተካተዋል።
የፍትህ ሚኒስትር ሀና አርዓያሥላሴ ከቻይና ሉዓላዊ ሕዝብ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዪንግ ዮንግ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱም ላይ ኢትዮጵያና ቻይና የቀደምት ሥልጣኔ ተምሳሌት እና 55 አመታት ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸው ተነስቷል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል የፍርደኞች ማዘዋወር እና በወንጀል ጉዳዮች የጋራ ትብብር የተደረጉ ስምምነቶችን ለመተግበር በሁለቱም ወገን እንደሚሰራ ተገልጿል።
በኢፌዴሪ ፍትህ ሚኒስቴር እና በቻይና ፍትህ ሚኒስቴር መካከል የአቅም ግንባታ ስራዎችን ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት የተፈረመ መሆኑን በማስታወስ በቀጣይ በበለጠ ትብብር ለመስራት ተስማምተዋል።
የቻይናው ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዪንግ ዮንግ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ መሆኗን አንስተው፤ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ጠንካራ ወዳጅነት በመጠቀም ቻይና ከአፍሪካ ጋር ላላት ግንኙነት እንደ መግቢያ በር እንደምትታይ አመልክተዋል።
በቀጣይ የቻይና መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖረውን ግንኙነት የበለጠ እንደሚያጠናክር መግለጻቸውን የፍትህ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መረጃ አስታውቋል።