ቀጥታ፡

መንግስት የትምህርት ስብራትን ለመጠገን የወሰዳቸው እርምጃዎችና የተከተላቸው ስትራቴጂዎች ውጤት አምጥተዋል 

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 18/2018(ኢዜአ)፦መንግስት የትምህርት ስብራትን ለመጠገን የወሰዳቸው እርምጃዎችና የተከተላቸው ስትራቴጂዎች ውጤት አምጥተዋል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ  አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡


 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2017 ዓ.ም አገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወስደው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች እውቅናና ሽልማት ሰጥቷል፡፡

ሽልማቱን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለተማሪዎቹ አስረክበዋል።


 

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት፣ መንግስት የትምህርት ስብራትን ለመጠገን አዲስ ፖሊሲ እና ሥርዓተ ትምህርት በመቅረጽ ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል፡፡

ይህም የመማር ማስተማር ሥርዓቱን ምቹ በማድረግ እና የትምህርት ግብዓቶችን በማቅረብ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል፡፡

መንግስት የትምህርት ስብራትን ለመጠገን የወሰዳቸው እርምጃዎችና የተከተላቸው ስትራቴጂዎች የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ረገድ ውጤት አምጥተዋል ብለዋል፡፡

የተማሪዎች ውጤት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ እና እያደገ መምጣቱን ነው የተናገሩት፡፡


 

በአገር አቀፍ ደረጃ የተመዘገበው ውጤት ለዘርፉ ትኩረት ከተሰጠ የትምህርት ጥራትንና ተደራሽነትን በአጭር ጊዜ ማሳካት እንደሚቻል ትልቅ ማሳያ ነው ብለዋል።

በቀጣይ የመጣውን ውጤት እያበረታታን ለሌላ ስኬት ጠንክረን የምንሠራ ይሆናል ነው ያሉት።

ተማሪዎች ዛሬ የተሰጣቸው ሽልማት በቀጣይ ሕይወታቸው ጠንክረው በመስራት ለአገራቸው የበኩላቸውን የላቀ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በ2017 ዓ.ም የተመዘገበው ውጤት መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት ትሩፋት ነው ብለዋል፡፡


 

ለተገኘው ውጤት የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ወሳኝ ሚና ማበርከቱን አንስተዋል፡፡

በ2018 ዓ.ም ከዚህ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ቢሮው ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ለተግባራዊነቱም ባለድርሻ አካላት ትብብራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡

ኢዜአ ካነጋገራቸው ተሸላሚ ተማሪዎች መካከል ናኢም ለገሰ፤ሽልማቱ ለቀጣይ ህይወቴ ስንቅ የሚሆንና ከኛ ቀጥለው ለሚመጡ ተማሪዎች ደግሞ ተስፋ የሚሆን ነው ብሏል፡፡


 

ሌላኛው ተሸላሚ ተማሪ ዳዊት ፈይሳ በበኩሉ፤ እውቅናው እኛ እንድንበረታ እና በቀጣይ ለሀገራችን የተሻለ ስራ እንድንሰራ የሚያነሳሳን ነው ብሏል፡፡


 

ከተማ አስተዳደሩ የሰጠን እውቅና ሃላፊነት እንዲሰማንና ለበለጠ ስራ እንድንተጋ ያደርገናል ያለችው ደግሞ ሌላኛዋ ተሸላሚ ተማሪ እየሩሳሌም ያየሰው ናት፡፡


 

ለተመዘገበው የተማሪዎች የላቀ ውጤት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማትና የትምህርት ማኅበረሰብ አባላት እውቅና ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም